በኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ እስካሁን ምን ተሰራ?
ባለፉት አምስት ዓመታት በመጀመሪያ ምእራፍ 25 ቢልዮን ችግኞችን ተተክለዋል
ዘንድሮ 6.5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን፤ ሀምሌ 10 በአንድ ቀን 500 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ቀጠሮ ይዛለች
ኢትዮጵያ “አረንጓዴ አሻራ” ብላ የሰየመችው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማካሄድ ከጀመረች ዘንድሮ 5ኛ ዓመት ላይ ትገኛለች።
ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ባካሄደችው የመጀመሪያ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም 25 ቢሊየን ችግኞችን መትከሏን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ሁለተኛ ምእራፍ የተጀመረ ሲሆን በዚህኛው ምእራፍም 25 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል አቅዳለች፤ ዘንድሮ ማለትም በ2015 ዓ.ም 6.5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል አቅዳለች። የዘንድሮ የችግኝ ተከላ ከተጀመ አንስቶ እስከ ሰኔ 29 2015- 900 ሚሊየን ችግኝ ተተክሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የፊታችን ሐምሌ 10 2015 ዓ.ም በአንድ ቀን 500 ሚልዮን ችግኞች ለመትከል ቀጠሮ የያዘች ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ታሪክ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።