አቡዳቢ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን “የአረንጓዴ ሃይድሮጅን ጉባኤ” እያስተናገደች ነው
ጉባኤው የመሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችን እና ባለሙያዎችን ያሳተፈ ነው ተብሏል
የጉባኤው አዘጋጅ አረንጓዴ ሃይድሮጅን ለማምረት እየታተረ ያለው የአቡ ዳቢው ማስዳር ኢነርጂ ኩባንያ ነው
አረብ ኢሚሬትሷ አቡ ዳቢ ‘የዘላቂነት ሳምንት 2023’ ብላ በሰየመችው መርሃ ግብር በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን “የአረንጓዴ ሃይድሮጅን ጉባኤ” እያስተናገደች ነው፡፡
በአቡ ዳቢው ማስዳር ኢነርጂ ኩባንያ አማካኝነት የተዘጋጀው ጉባኤው የአረንጓዴ ሃይድሮጂን ዘርፍን ማጎልበት ያለውን ጠቀሜታ እና ሀገራት በአየር ንብረት መስክ ግባቸውን ለማሳካት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደረገፍ ትልቅ ሚና ያለው ነው ተብሏል፡፡
“ግሪን ሃይድረጅን ሳሚት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጉባኤ የሀገራት መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ባለሙያዎችን፣ ባለሀብቶችን፣ ስራ ፈጣሪዎችን እና ወጣቶችን ከዓለም ዙሪያ በማሰባሰብ ተከታታይ ገንቢ ውይይቶችን የሚያደረጉበት ሲሆን ለኮፕ-28 ጥሩ መሰረት የሚጥል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ጉባኤው በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ውስጥ የሚካሄዱ በሃይድሮጂን ኢኮኖሚ ልማት ላይ ያተኮሩ ከፍተኛ ደረጃ ስብሰባዎችን ያካትታም ነው የተባለው፡፡
የአቡ ዳቢ የዘላቂነት ሳምንት ዋና አዘጋጅ ማስዳር በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የአረንጓዴ ሃይድሮጂን ኢኮኖሚ ግንባታን ለመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ በማሰብ አዲስ አረንጓዴ ሃይድሮጅን ዲፓርትመንት መቋቋሙን በታህሳስ ወር አስታውቆ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በበርካታ አረንጓዴ ሃይድሮጂን ፕሮጄክቶች ውስጥ የሚሳተፈው ማስዳር በ 2030 አንድ ሚሊዮን ቶን አረንጓዴ ሃይድሮጅን በየዓመቱ ለማምረት አቅዶ እየሰራ መሆኑም ይታወቃል፡፡
ለዚህም እንደፈረንጆቹ በ2030 እስከ 480ሺህ ቶን አረንጓዴ ሃይድሮጅን በ 4 ጊጋ ዋት ኤሌክትሮላይዘር ለማምረት በማቀድ በግብጽ ውስጥ አረንጓዴ ሃይድሮጅን ማምረቻ ፋብሪካዎችን ለማልማት በመንግስት ከሚደገፉ መሪ የግብጽ ተቋማት ጋር ለመተባበር ስምምነት ተፈራርሟል።