ኢትዮጵያ ከቻይና የተበረከተላትን 300 ሺህ ዶዝ ሲኖፋርም የኮቪድ-19 ክትባት ተረከበች
ድጋፉ ኢትዮጵያ 20 በመቶ ዜጎችን ለመከተብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ያግዛል- ዶ/ር ሊያ ታደሰ
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም 2 ነጥብ 2 ሚሊየን አስትራ ዜኒካ ክትባቶችን ተረክባለች
የቻይና መንግስት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ያደረገው 300 ሺህ ዶዝ ሲኖፋርም የተሰኘ የኮቪድ-19 ክትባት ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል።
ክባቱንም በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢውሃን ለጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።
በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይም የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደኤታ አምበሳደር ቡርቱካን አያኖ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ቻይና ላደረገችው ድጋፍ አመስግነው፤ ሀገሪቱ ዛሬ ካደረገችው ድጋፍ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የኮቪድ19 መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጓን አስታውሰዋል፡፡
ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የክትባት ሂደት ለማጠናከር እና እንደ ሀገር 20 በመቶ ዜጎችን ለመከተብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢውሃን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ቻይና በኮቪድ19 በተጠቃች ጊዜ አጋርነቷን ያሳየች ጠንካራ አጋር መሆኗን አውስተዋል።
አምባሳደሩ በቀጣይም ቻይና የኢትዮጵያውንን ህይወት ከወረርሽኑ ለመታደግ በሚደረገው ጥረት ክትባቶችን ጨምሮ መሰል ድጋፎችን እንደምታደርግም አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመቋቋም ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ እና የዝጎቸዋን ህይወት ለመቀየር በምታደርገው ጥረት ውስጥም ቻይና ሁሌም ከጎኗ ነች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በኮቫክስ ጥምረት በኩል 2 ነጥብ 2 ሚሊየን አስትራ ዜኒካ ክትባቶችን መረከቧ ይታወሳል።
ከሁለት ሳምንታት በፊትም ዜጎቿን መከተብ የጀመረች ሲሆን፤ እስከ መጭው ታህሳስ 2014 ዓ.ም ድረስ 20 በመቶ የሚሆነውን ህዝቧን ለመከተብ ማቀዷን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በወቅቱ አስታውቋል።