ፈቃዱ ‘ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ’ ለተባለ ለአራት የግል የቴሌኮም ኩባንያዎች ስብስብ የተሰጠ ነው
በኢትዮጵያ ከ126 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው የግል የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ተሰጠ፡፡
ፈቃዱ ያለፉትን 126 ዓመታት የቴሌኮምና ተያያዥ ግልጋሎቶችን በበላይነት ይዞ ሲያስተዳድር በነበረው በኢትዮጵያ መንግስት ነው ‘ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ’ ለተባለ ለአራት የግል የቴሌኮም ኩባንያዎች ስብስብ የተሰጠው፡፡
‘ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ’ የኬንያውን ሳፋሪ ኮም፣የደቡብ አፍሪካውን ቮዳኮም፣ የእንግሊዙን ቮዳፎን እና የጃፓኑን ሱሚቶሞን እንዲሁም ሲዲሲ ግሩፕ የተሰኘ የዩናይትድ ኪንግደም የልማት ማዋዕለ ነዋይ አቅራቢ ተቋምን ያካተተ ነው፡፡
የፈቃዱን መሰጠት በማስመልከትም ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ/ም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ እና የኬንያ መሪዎች እና ሌሎችም ከፍተኛ የሃገራቱ ባለስልጣናት በተገኙበት ይፋዊ የስምምነት ፊርማ ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡
“በ2010 ዓም ሀገር የማስተዳደር ኃላፊነትን ስረከብ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፉን ወደግል ለማዛወር እና ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ባለ ሀብቶች ለመክፈት ያለኝን ቁርጠኝነት ገልጬ ነበር” የሚል ስምምነቱን የተመለከተ መልዕክት ከይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ያሰፈሩት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ “ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ ያስተዋወቀ ነበር” ብለዋል፡፡
“ዛሬ ከግሎባል ፓርትነርሺፕ ለኢትዮጵያ ጋር ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን ለማጽናት የሚያስችለንን ታሪካዊ ስምምነት ተፈራርመናል”ም ብለዋል ጠ/ሚ ዐቢይ፡፡
የፋይናንስ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ስምምነቱ የተፈረመበትን የትናንትናውን ቀን ለኢትዮጵያውያን በልዩ እና ጠቃሚ ቀንነት አንስተዋል፡፡
እርምጃውን ገና በጅምርነት የጠቀሱም ሲሆን ዘመናዊ የቴሌኮም ግልጋሎቶችን የሚሰጥ ተቋም ለመገንባት ከተለያዩ የግል አጋሮች ጋር በትብብር መስራቱ እንደሚቀጥል መነገራቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡
የመጀመሪያው የግል የቴሌኮም ኦፕሬተር ሆኖ በኢትዮጵያ የሚሰማራው ስብስቡ ላገኘው የአገልግሎት ፈቃድ 850 ሚሊዬን ዶላር ለመንግስት ከፍሏል፡፡
በቀጣዮቹ 10 ዓመታት 8 ነጥብ 5 ቢሊዬን ዶላር ገደማ ገንዘብን በዘርፉ ፈሰስ በማድረግ አዳዲስ አገልግሎቶችንና መሰረተ ልማቶችን እንደሚያቀርብም ይጠበቃል፡፡