ኮሚሽነር ዳንኤል ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላደረጉት አስተዋጽኦ ሽልማቱ እንደተበረከተላቸው ተገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ ቅጥር ግቢ በተካሄደ የሽልማት ሥነ ሥርዓት የአውሮፓ ኅብረት ሹማን ሽልማት (Schuman EU Awards) ተበርክቶላቸዋል።
ሽልማቱ በኢትዮጵያ ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተባለ ሲሆን ለመጀ ሽልማቱ “ዴሞክራሲን፣ የሕግ የበላይነትን፣
ሰብአዊ መብቶችን፣ መቻቻልን እና እኩልነትን በማስፋፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰዎች” ዕውቅና የሚሰጥ ነው ተብሏል።
የአውሮፓ ኅብረት ሹማን ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ የተበረከተው እ.ኤ.አ. በ2017 በምያንማር የኅብረቱን 60ኛ ዓመት ምሥረታ በማስመልከት ነበር።
ሽልማቱ ሰዎችን ለማበረታታት እና ተግባቦትን በማጠናከር ዲፕሎማሲን በተሻለ መንገድ ለመከወን ያለመ ሲሆን የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር “የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረትን በአንድነት ከሚያቆሙት ጉዳዮች መካከል ዋናው ነው ብለዋል።
ሰብአዊ መብቶችን መጠበቅ እና ማስፋፋት ያለውን ጥቅም እንረዳለን ያሉት አምባሳደር ካቢያ የአውሮፓ ኅብረት ፍጹም እንዳልሆኑ ቢገነዘብም የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሂደቶቹን እና የማስፋፋት ስልቶቹን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በፈረንሳዊው ፖለቲከኛ፣ ምሁር እና አክቲቪስት ሮበርት ሹማን ስም የተሰየመው ይህ ሽልማት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የአውሮፓውያንን እና የትራንስ አትላንቲክ ተቋማትን በመገንባት ጉልህ አስተዋጽዖ ከነበራቸው እና የአውሮፓ ኅብረትን የአውሮፓ ምክር ቤት እና የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት መሥራቾች መካከል አንደኛው ናቸው።
ሽልማቱ መቻቻል እና ነጻነትን በማስፋፋት ረገድ ለተከናወኑ የላቁ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን፣ “እነዚህን ሁሉን አቀፍ እሴቶች በተቃውሞ እና በትችት ውስጥም ቢሆን በጽናት ለኖሩ እና ለደገፉ ከፍተኛ ስብዕና ላላቸው ሰዎች" ዕውቅና የሚሰጥ ነው።
አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ሽልማቱን ለዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባበረከቱበት ወቅት ዶ/ር ዳንኤል የሚመሩት ኢሰመኮ የደረጃ “A” ዕውቅና (ወይም አንደኛ ደረጃ እውቅና ያለው ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሆኗል፤ ይህም በራሱ አስደናቂ ስኬት ነው። ኢሰመኮ አሁንም በተግዳሮቶች እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ጭምር ድምጽ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል።
ዝግጅቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች በተገኙበት በአዲ አበባ ተካሂዷል።
የዘንድሮው የአውሮፓ ኅብረት የሹማን ሽልማት ከተቀበሉት መካከል:-
• ጋሪ ኢስማኤል ዩሱፍ - የሆርሙድ የሴቶች ማኅበር መሪ፣
• ጌቱ ሳቀታ - የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብቶች ሊግ መሥራች፣
• መላኩ በላይ - የፈንዲቃ የባህል ማእከል መሥራች፣
• መልካሙ ኦጎ - የቁም ለአካባቢ ሊቀ-መንበር፣
• የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣
• ያሬድ ኃይለማርያም- የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማእከል ዋና ዳይሬክተር ይገኙበታል።
በተጨማሪም በሰብአዊ መብቶች ሥራዎቻቸው ምክንያት በእስር ቤት ውስጥ ወይም በስደት ላይ ለሚገኙ እና ይህንን ሽልማት በአካል ለመቀበል ላልቻሉ ኢትዮጵያውያን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች በሙሉ የዕውቅና ተሰጥቷል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት እንዳሉት ሽልማቱ “ኢሰመኮ እንደ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም የተሰጠውን ኃላፊነት በተሟላ መልኩ ለመወጣት እያደረገ ላለው ጥረት ዕውቅና የሚሰጥ እና ለሕዝብ ያለብንን ኃላፊነት በትሕትና እና በቅንነት እንድንሸከም የሚያበረታታን በመሆኑ ነው” ብለዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር እ.ኤ.አ. የ2021 “ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሕይወት ዘመን ትግላቸው” የጀርመን አፍሪካ ሽልማትን እንዲሁም የአሊሰን ዴስ ፎርጅስ ልዩ የሰብአዊ መብቶች አክቲቪዝም ሽልማትን ጨምሮ ከሌሎች ብሔራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅናዎችን ማግኘታቸው ይታወሳል።