ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የሱዳን ስደተኞች የደህንነት እና የመሰረታዊ አቅርቦቶች ችግር እንዳለባቸው ተናገሩ
በሱዳን ባለፈው አመት ሚያዝያ አጋማሽ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ተሰድደዋል
ኤጀንሲው የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ኩመር እና አውላላ የተባሉ የስደተኞች ካምፖችን ለመጠበቅ ተጨማሪ ጸጥታ ኃይል መድቧል ብሏል
ኢትዮጵያ ውስጥ ከካምፕ ውጭ የሚኖሩ የሱዳን ስደተኞች የደህንነት ስጋት እና የመሰረታዊ አቅርቦቶች ችግር እንዳጋጠማቸው ተናገሩ።
በሱዳን ባለፈው አመት ሚያዝያ አጋማሽ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ተሰድደዋል።
ሱዳናውያን ስደተኞች በኢትዮጵያ፣ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ኩመር እና አውላላ በተባሉ ሁለት የስደተኞች መጠለያ ካሞፖች ሰፍረው ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ በአውላላ የመጠለያ ካምፕ ላይ በደረሰ ጥቃት እና በመሰረታዊ አቅርቦት ማነስ ምክንያት በፈረንጆቹ ባለፈው ግንቦት አንድ 1000 ስደተኞች ካምፑን ለቀው መውጣታቸውን የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ገልጿል።
ከአውላላ ወጥተው በጫካ ውስጥ ያሉት ስደተኞች አሁንም የመሰረታዊ አቅርቦቶች እና የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ።
"እንደምታየው ጫካ ውስጥ ነው ያለነው። እዚህ ቦታ ለህይወት አስፈላጊ የሆኑት ምግብ፣ ውሃ፣ ጥበቃ ሳይደረግልን 14 ቀን ሆኖናል" ሲል አንድ ተፈናቃይ ለአል ዐይን ተናግሯል።
ሌሊቱን ሙሉ ዝናብ ላይ እያሳለፍን ነው ያለው ይህ ተፈናቃይ "ነፍሰ ጡሮች እና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አካል ጉዳተኞች ከእኛ ጋር አሉ" ብሏል።
አለምአቀፉ ማህበረሰብ ተፈናቃዮቹ ያሉበትን ቦታ እንዲያይላቸው እና እንዲረዳቸውም ተፈናቃዩ ተማጽኗል።
ሌላኛዋ በዚሁ ጫካ ያለች ሴት ተፈናቃይም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንደሆነች ትገልጻለች።
"የደህንት ጥበቃ የለንም፣ ምንም ነገር የለንም፤ እርዱን" ስትል ተናግራለች።
የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ በአውላላ የተፈናቃዮች ካምፕ አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ መንገድ ዳር የሚገኙ የሱዳን ተፈናቃዮች ጉዳይ እንደሚያሳስበው በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኤጀንሲው ከተፈናቃዮቹ ውስጥ የተወሰኑት የረሃብ አድማ ማድረጋቸውን እና ይህም ስጋት ውስጥ እንደከተተው በመግለጫው ጠቅሷል።
የስደተኞችን የተሻለ አገልግሎት እና የደህንነት ጥበቃ የማግኘት ጥያቄ እንደሚረዳ የገለጸው ኤጀንሲው የለሚነሱ ችግሮች መፍትሄ ለማግኘት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል።
ኤጀንሲው ወደ ቦታው በመሄድ ስደተኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማየት ችሎ የነበረ ቢሆን ድጋሚ ለመሄድ ያደረገው ሙከራ ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶች ተስተጓጉሏል ብሏል።
ኤጀንሲው ለእነዚህ ስደተኞች ምግብ፣ ውሃ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንደሚያቀርብ እና አውላላ የስደተኞች ካምፕም ለእነሱ ክፍት መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለእነዚህ ስደተኞች ካምፓቸውን ከለቀቁ ጀምሮ ጥበቃ እያደረገላቸው ነው ብሏል ኤጀንሲው።
ነገርግን መሬት ላይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለቡድናችን እና ለሰብአዊ እርዳታ ሰራኞቻችን ፈታኝ መሆኑን ኤጀንሲው ጠቅሷል።
ኤጀንሲው እንደገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ኩመር እና አውላላ የተባሉትን የስደተኞች ካምፖች ለመጠበቅ ተጨማሪ ጸጥታ ኃይል መድቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት ግን ስለስደተኞቹ በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም።
ከፈረንጆቹ ሚያዝያ 2024 ጀምሮ በኩመር የመጠላያ ካምፕ 6000 በዋናነት የሱዳን፣ የኤርትራ እና የደቡብ ሱዳን ተፈናቃዮች ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን በአውላላ ደግሞ 2000 የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ተፈናቃች ይገኛሉ።