“…ከመቀሌ ወደ ሓውዜን ለመሄድ 40 እና 60 ብር እንከፍል ነበር፤ አሁን ግን ከ600-1000 ብር እየከፈልን ነው” ያሉ ነዋሪ የዋጋ ንረቱን አማረዋል
ባለፈው ጥቅምት 24፣2013ዓ/ም በፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በትግራይ ክልል ሰብአዊና ኢኮኖሚያ ቀውስ መከሰቱ ይታወቃል፡፡
በግጭቱ ሳቢያ የክልሉ ዋና ከተማ መቀሌ ነዋሪዎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸውን አል ዐይን አማርኛ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ከግጭቱ በኋላ ነዋሪዎቹ የመሰረታዊ ሸቀጦችና የትራንስፖርት ዋጋ በከፍተኛ መጠን መናሩን ገልጸዋል፡፡
በሹፍርና ሙያ የተሰማሩት አቶ አብርሀ፣ የጀበና ቡና በመሸጥ የሚተዳደሩት ወ/ሮ ራሄል እንዲሁም በግል ስራ የተሰማሩት ወ/ሮ ሄለን የተባሉ የመቀሌ ነዋሪዎችን አል ዐይን አማርኛ አነጋግሯል፡፡
እንደ ነዋሪዎቹ ከሆነ ከግጭቱ በኋላ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በተለይም የኮንስትራክሽን ዘርፉ እጅጉን ተቀዛቅዘዋል፤ የኑሮ ውድነቱም ጣራ መንካቱን ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ከግጭት ማግስት በመጀመርያዎቹ ቀናት በብሄራዊ ባንክ “በትግራይ የተከፈቱ አካውንቶች እንዲዘጉ የማድረግ ውሳኔ መተላለፉ በሀብታሙም ሆነ ድሀው የህብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ተፅእኖ የፈጠረ ነበር” ብለዋል፡፡
የጸጥታው ሁኔታ ትንሽ ሲረጋጋ ተዘግተው የነበሩ አካውነቶች የተከፈቱ ቢሆንም፣ የዋጋ ንረቱ አይሎ ነዋሪዎቹ መቋቋም እንዳቃታቸው ተናግረዋል፡፡
ከግጭቱ በኋላ የትራንስፖርት ዋጋ ንረት
አቶ አብርሀ በትራንስፖርት ዘርፉ “ከመቀሌ-ሽረ እንዲሁም ከመቀሌ-አላማጣ ለመጓዝ የትራንስፖርት ዋጋ እስከ 1ሺ 500 ብር ደርሶ ነበር” ብለዋል፡፡
“ቀደም ሲል ከመቀሌ ወደ አዲግራት እንዲሁም ከመቀሌ ወደ ሓውዜን ለመሄድ 60 እና 40 ብር እንከፍል ነበር፤ አሁን ግን ከ600 እስከ 1000 ብር እየከፈልን ነው” በማለት አሁንም ድረስ ያልተቀረፈውን የዋጋ ጭማሪ ችግር እንደ አብነት አንስተዋል አቶ አብርሀ፡፡
የአቶ አብርሀን ሀሳብ የሚጋሩት ወ/ሮ ራሄልና ወ/ሮ ሄለን በበኩላቸው፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፉ በየጊዜው የሚለዋወጥና አሰራር ያልተበጀለት ስለሆነ አቅም የሌላቸው ሰዎች ከቤተሶቦቻቸው ጋር ምንም አይነት ኮሚዩኒኬሽን ስላልነበራቸው የቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ በረሀ በማሳበር የእግር ጉዞ እንደሚደርጉም ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርቱ ዋጋ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ካስቀመጠው ታሪፍ የ35 በመቶ በላይ ጭማሪ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
ከግጭቱ በኋላ የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ንረት
በአስቤዛዎች በአነስተኛ የምግብ ፍጆታ ሸቀጦች ላይ እንደየአይነታቸው ከ100 እስከ 150 ብር የዋጋ ጭማሪ መታየቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ቀደም ሲል በኩንታል ከ4ሺ500 ብር አስከ 5000 ብር ይሸጥ የነበረ ጤፍ አሁን በተወሰነ መልኩ ቢስተካከልም ከ7ሺ 500 ብር አስከ 8000 ብር የደረሰበት ወቅት ነበርም ብለዋል፡፡
ለተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ አሁንም ቢሆን በከተማው ያለው ያልተረጋጋ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት መሆኑንም ነዋሪዎቹ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
ዝርፊያ ይኖራል በሚል ስጋት፣ የልብስ መሸጫ ቤቶች /ቡቲኮችን/ ነዋሪዎቹ እንደ አብነት ያነሱ ሲሆን ፤ አሁን ላይ የቡቲክ ባለቤቶች ማታ ማታ የሚሸጡትን ልብስ በባጃጅ ጭነው ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱና ጠዋት ደግሞ ጭነው እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡ ይህ በራሱ ለዋጋ ጭማሪው ራሱን የቻለ ምክንያት መሆኑን በማንሳት፡፡
ቀደም ሲል በግጭት ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የአቅርቦት ችግር እንደነበር ይህም ከነበረው የአሰራር ክፍተት ጋር ተዳምሮ ህዝቡ ለከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲዳረግ ምክንያት ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ፣ አሁን ላይ የአቅርቦቱ ችግር መቀረፉን ግን ደግሞ በጣም የላላ አሰራርና የቁጥጥር ስርአት መኖሩ ለህገ-ወጥ ስራዎች አመቺ እንደሆነና የኑሮ ውድነቱም እንዳለ ሊቀጥል እንደቻለ ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ክልሉን የሚያስተዳድረው ጊዜያዊ አስተዳደር የቁጥጥር ስርአቱን እንዲያጠክርና ሰላም እንዲያሰፍን ጠይቀዋል፡፡
የፌደራል መንግስት የትግራይን ክልል የሚያስተዳድረው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን አሳውቆ ባካሄደው የ“ህግ ማስከበር ዘመቻ” ህዳር 19 የክልሉን ዋና ከተማ መቆጣጠሩንና ዘመቻው ማብቃቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ ዶ/ር ሙሉ ነጋ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በተወሰኑ ኪስ ቦታዎች ላይ አሁንም ውጊያ መኖሩንና ያልተያዙ ቦታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግስት በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቁሉ ሰዎች 70 በመቶ የሚሆን እርዳታ እያደረሰ መሆኑን እና 30 በመቶ የሚሆነው በለጋሾች መሸፈኑን ገልጿል፡፡ ክልሉን ክፍት እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ጫና ሲደረግበት የነበረው መንግስት፣ ለዓለምአቀፍ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ክፍት ማድረጉን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡