ከተፈፀሙ 285 የሳይበር ጥቃቶች መካከል 121ዱ በአጥፊ ሶፍትዌሮች (Malware) የተፈጸሙ ጥቃቶች ናቸው
ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ 285 የሳይበር ጥቃቶች ተፈጽመዋል
በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 6 ወራት በተለያዩ ቁልፍ የሀገሪቱ መሰረተ-ልማቶች ላይ የተነጣጠሩ 285 የሳይበር ጥቃቶች መከሰታቸውን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የብሔራዊ ሳይበር ድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ ዲቪዥን (ኢትዮ-ሰርት) አስታውቋል፡፡
በግማሽ አመቱ ከተፈፀሙ 285 የሳይበር ጥቃቶች መካከል 121ዱ ወይም 42.5 ከመቶው በአጥፊ ሶፍትዌሮች (Malware) የተፈጸሙ ጥቃቶች ናቸው፡፡
በዚሁ ጊዜ ውስጥ 48 የድረ-ገፅ ጥቃቶች፣ 32 የመሠረተ ልማት ቅኝቶች፣ 75 ወዳልተፈቀደ ሲስተም ሰርጎ የመግባት ተግባር፣ 8 የሳይበር መሠረተ-ልማቶችን ሥራ የማቋረጥ ሙከራዎች እና 1 የሳይበር ማጭበርበር ጥቃት መከሰታቸው ታውቋል፡፡
በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያው 6 ወር 140 የሳይበር ጥቃት የተከሰተ ሲሆን በያዝነው ዓመት ቁጥሩ ወደ 285 ከፍ ብሏል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የጥቃት መጠኑ በእጥፍ ጨምሯል፡፡
በሀገራችን እየጨመረ ላለው የሳይበር ጥቃት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ግለሰቦች እና ተቋማት መጨመር፣ ወንጀለኞች በዘርፉ ያላቸው ፍላጎት ማደግ፣ በሀገራችን ስለ ሳይበር ጥቃት ያለው የግንዛቤ መጠን ዝቅትኛ መሆን እና ለሳይበር ደህንነት የሚሰጠው ትኩረት ማነስና ቸልተኝነት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ኤጀንሲው በሰራው ስራ የሀገራችን ቁልፍ መሰረተ-ልማቶችን ዒላማ አድርገው የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ጉዳት ሳያደርሱ ለማክሸፍ ተችሏል፡፡
በሀገራችን ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ በመከላከል እና ተከስተው ሲገኙም የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸዉ በፊት በአፋጣኝና በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት ረገድ ኤጀንሲው አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡