ልዩልዩ
"ሳይበር ሆርስ ግሩፕ" ከግድቡ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ በድረ-ገጾች ላይ የመበርበር ሙከራ ሲያደርግ ነበረ- ኢመደኤ
ግሩፑ 37‚000 በሚደርሱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኮምፒውተሮች ላይ አዲስ ቫይረስ ለመልቀቅ መዘጋጀቱም ተገልጿል
የሳይበር ምህዳሩ ተጠቃሚዎች ተገቢውን የሳይበር ደህንነት ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተጠቁሟል
"ሳይበር ሆርስ ግሩፕ" የተሰኘ የመረጃ ሰርሳሪ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ኮምፒውተሮች ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ማድረጉ እንደተደረሰበት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው በትናትናው እለት ባወጣው መረጃ ይህ የመረጃ ሰርሳሪ ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ኮምፒውተሮች ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈፀም ሙከራዎችን እደረገ ነው ብሏል።
"ሳይበር ሆርስ ግሩፕ" የተሰኘ የመረጃ ሰርሳሪ ቡድን አዲስ የኮምፒውተር ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ኮምፒውተሮች ላይ ለመልቀቅ ዝግጅት ማድረጉንም ደርሼበታለሁ ብሏል ኤጀንሲው።
ይህ ቫይረስ "ብላክ ፒራሚድ ዋር" የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን 37‚000 በሚደርሱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኮምፒውተሮች ላይ ማነጣጠሩ ተገልጿል፡፡
ይህ ቡድን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ በተለያዩ የኢትዮጵያ ድረ-ገጾች ላይ የመበርበር ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱንም ኤጀንሲው ገልጿል።
በመሆኑም ሁሉም የሳይበር ምህዳሩ ተጠቃሚዎች ተገቢውን የሳይበር ደህንነት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አሳስቧል።