የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ የተጀመረው ስራ እስከ ቀጣዩ ሰኔ ወር እንደሚጠናቀቅ ጠ/ሚኒስትሩ ገለጹ
ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የስኳር ፋብሪካዎች ለውጭ እና ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከሚሸጡ ተቋማት መካከል ናቸው
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር ጫና ካለባቸው አገራት ዝርዝር ውስጥ መካተቷ ተጨማሪ ብድር እንዳታገኝ እንቅፋት መሆኑን ጠ/ሚ ዐቢይ ተናግረዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ እንዳሉት ፣ መንግስት የገጠመውን የበጀት እጥረት ለመፍታት ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ሌሎች የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ለመሸጥ የወሰነውን ውሳኔ በጥንቃቄ በማስኬድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ 40 በመቶ ለመሸጥ ጨረታ ማውጣቱን አስታውሰው አጠቃላይ ስራው እስከ ቀጣዩ ሰኔ ወር ድረስ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የስኳር ፋብሪካዎች እና ሌሎች የልማት ድርጅቶች ለውጭ እና ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከሚሸጡ ተቋማት መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር ጫና ካለባቸው የዓለማችን አገራት ዝርዝር ውስጥ መካተቷ ተጨማሪ ብድር እንዳታገኝ እንቅፋት እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢኮኖሚውን ከብድር ጫና ለማላቀቅም የአገር ውስጥ ቁጠባን ማሳደግ፣ የመንግስትን ያልተገባ ወጪ መቀነስ፣ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ማሻሻል፣ ለግሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ የብድር አቅርቦቶችን ማሳደግ እና የወጪ ንግድን ማሳደግ “ከጫናው ለመላቀቅ ብቸኛ አማራጮች ናቸው” ብለዋል።
ከዚህም አንጻር ኢኮኖሚውን ከብድር ጫና ለማላቀቅ ፣ በ2010 ዓ.ም ዓመታዊ ኢኮኖሚው የብድር ጫናው የ37.6 በመቶ አስተዋጽኦ ነበረው።
በ2011 ዓ.ም ደግሞ የብድር ጫናውን ወደ 29 ነጥብ 4 በመቶ ዝቅ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በ2012 ዓ.ም ወደ 26 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከፍተኛ የብድር ጫና ካለባቸው አገራት ውስጥ የተመደበች ሲሆን መካከለኛ የብድር ጫና ካለባቸው አገራት ጎራ ለማሰለፍ እየተሰራ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
የዜጎችን ቁጠባ ለማሳደግ በተሰራው ስራ ባለፉት 8 ወራት ውስጥ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የባንክ ሂሳብ ከፍተው ከ98 ቢሊዮን በላይ ብር መቆጠባቸውን በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡
በዚህም የዜጎች የቁጠባ መጠን በ25 በመቶ ማደጉን የጠቀሱ ሲሆን የብድር አቅርቦት ደግሞ በ28 በመቶ እንዳደገ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ተናግረዋል።