“የኮንጎ ልዑክ በግድቡ ዙሪያ ለመወያየት ይመጣል ብለን እየጠበቅን ነው”- ዲና ሙፍቲ
ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረስ ወደ ትግራይ በፍቃድ ይገቡ የነበሩ የረድዔት ተቋማት አሁን ላይ በማሳወቅ ብቻ እየገቡ መሆኑንም ገልጸዋል
ቃል አቀባዩ የግድቡ የሶስትዮሽ ውይይት በቅርብ ሊጀመር እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል
የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የሆነችው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ልዑክ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው ግድብ ዙሪያ ለመወያየት ሊመጣ እንደሚችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ስለግድቡ ለመወያየት ከኪንሻሳ የሚመጣ ልዑክ ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ የግድቡ የሶስትዮሽ ውይይት በቅርብ ሊጀመር እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
አለመተማመን በማስቀረት ከሱዳንና ግብጽ ጋር በቅን ልቦና ለመደራደር በኢትዮጵያ በኩል አሁንም ዝግጁነት እንዳለም አንስተዋል አምባሳደር ዲና፡፡
አፍሪካ በህብረቱ ተወክላ ሊኖራት ስለሚችለው የአደራዳሪነት ሚና በተመለከተም ገልጸዋል፡፡
“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለው የኢትዮጵያ አቋም አሁንም እንደተጠበቀ ነው ያሉም ሲሆን ድርድሩ “ተስፋ ሰጪና የምንፈልገውን ነገር የምናገኝበት” እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለንም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት “የጦርነት አታሞን ከመደለቅ ይልቅ መወያየቱ” እንደሚበጅም ነው አምባሳደር ዲና የተናገሩት፡፡
በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከዚህ ቀደም በፍቃድ ይገቡ የነበሩ ዓለም አቀፍ የረድዔት ተቋማት አሁን ላይ በማሳወቅ ብቻ እየገቡ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡