አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከተሞች ያጋጠመው የነዳጅ እጥረት በቀጣዮቹ 2 ቀናት እንደሚቀረፍ ተገለጸ
በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ዛሬ እና ነገ የነዳጅ እጥረቱ እንደሚፈታ ድርጅቱ ለአል ዐይን ገልጿል
የነዳጅ እጥረት ያጋጠመው በአንድ ቀን የትራንስፖርት መስተጓጎል ምክንያት መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢዎች ድርጅት አስታውቋል
በአዲስ አበባ ካሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ቀናት ጀምሮ በነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎች እንደነበሩ አል ዐይን ታዝቧል።
የነዳጅ ሰልፉ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን እጥረቱ በከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ በማሳረፉ ምክንያት ፣ ታክሲ ፈላጊዎች እየተንገላቱ መሆኑን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረን ባደረግነው ምልከታ ታዝበናል።
የነዳጅ እጥረቱ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞችም አጋጥሟል።
አልአይን ዜና ለመሆኑ የነዳጅ እጥረቱ እንዴት ሊፈጠር ቻለ በሚል የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢዎች ድርጅትን ጠይቋል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም እንዳሉት ፣ አሁን ያለው የነዳጅ ዕጥረት የተከሰተው ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ መጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጠረ የጸጥታ ስጋት ምክንያት ነው።
ባለፈው ሳምንት በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በቦታ ይገባኛል ምክንያት ግጭት ተፈጥሮ የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
ይህ ግጭት ከሰዎች ህይወት ማለፍ ባለፈ ከጅቡቲ ወደቦች ወደ አገር ውስጥ ነዳጅ የማጓጓዝ ስራውን ለአንድ ቀን በማስተጓጎሉ የነዳጅ እጥረቱ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።
እጥረቱ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞችም ጭምር እንዳጋጠመ የገለጹት አቶ ታደሰ ፣ አሁን ላይ በቂ የሆነ ቤንዚን እና ናፍጣ ወደ አገር ውስጥ ስለገባ ችግሩ አይቀጥልም ብለዋል።
በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ በርካታ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ያስገቡ በመሆኑ ዛሬ እና ነገ የነዳጅ እጥረቱ እንደሚፈታም ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ከተሞች ደግሞ እስከ ማክሰኞ ባሉት ቀናት ውስጥ ያጋጠማቸው የነዳጅ ዕጥረት ይፈታል ብለዋል አቶ ታደሰ።
የጸጥታ ስጋት ባለባቸው ስፍራዎች ጭምር ነዳጅ በመቅረብ ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታደሰ በተለይም በመቀሌ ፣ ውቅሮ ፣ አላማጣ እና በዙሪያቸው ላሉ አካባቢዎች ነዳጅ መቅረቡንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አማካኝ ዕለታዊ የቤንዚን ነዳጅ ፍጆታ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ሲሆን ናፍጣ ደግሞ በቀን 8 ሚሊዮን ሊትር እንደሆነ የብሔራዊ ነዳጅ አቅራቢዎች ድርጅት መረጃ ያስረዳል።