በፓፑዋ ኒው ጊኒ በደረሰ የመሬት መንሸራተት 300 ሰዎች መቀበራቸው ተነገረ
የመሬት መንሸራተት አደጋው የደረሰው ባለፈው ሀሙስ እለት ነው ተብሏል
የፓፑዋ ኒው ጊኒ ጠረፍ ጠባቂ እንደገለጸው ከአውስትራሊያ በስተሰሜን በኩል በምትገኘው የፓሲፊክ ደሴት በተፈጠረው በዚህ አደጋ 300 ሰዎች እና 1182 ቤቶች ተቀብረዋል
በፓፑዋ ኒው ጊኒ በደረሰ የመሬት መንሸራተት 300 ሰዎች መቀበራቸው ተነገረ።
በፓፑዋ ኒው ጊኒ አንድ መንደር ባወደመው ከባድ የመሬት መንሸራተት አደጋ 300 ሰዎች እና 1100 ቤቶች መቀበራቸውን ሮይተርስ የሀገሪቱን ሚዲያዎች ጠቅሶ ዘግቧል።
ከዋና ከተማዋ ሞረስቢ 600 ኪሎሜትር ርቀት በምትገኘው የኢንጋ ግዛት ውስጥ የካዎካላም መንደር የመታው የመሬት መንሸራተት አደጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ሳይቀጥፍ እንደማይቀር ተሰግቷል።
እንደዘገባው ከሆነ የመሬት መንሸራተት አደጋው የደረሰው ባለፈው ሀሙስ እለት ነው።
የፓፑዋ ኒው ጊኒ ጠረፍ ጠባቂ እንደገለጸው ከአውስትራሊያ በስተሰሜን በኩል በምትገኘው የፓሲፊክ ደሴት በተፈጠረው በዚህ አደጋ 300 ሰዎች እና 1182 ቤቶች ተቀብረዋል።
የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ እና ንግድ ዲፓርትመንት በሙሊታካ ግዛት የሚገኙ ስድስት መንደሮችም በመሬት መንሸራተት አደጋው ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል።
ዲፓርትመንቱ "በፖርት ሞርስቢ የሚገኘው የአውስትራሊያ ከፍተኛ ኮሚሽን በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰውን ለመገምገም ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገረ ነው" ብሏል።
የነፍስ አድን ሰራተኞች እስካሁን የአራት ሰዎችን አስከሬን ያነሱ ሲሆን የሟቾች ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል።
የመሬት መንሸራተት አደጋው መንገዶችን በመዝጋቱ የነፍስ አድን ስራው በሄሊክፕተር ብቻ እየተከናወነ ይገኛል።
የፓፑዋ ኒው ጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሰ ማርፔ የአደጋ ጊዜ ባለስልጣናት፣ የመከላከያ ኃይል እና የመንገዶች ዲፓርትመንት ነፍስ ለማትረፍ በጥምረት እየሰሩ ነው ብለዋል።