መንግስት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ጥሎት የነበረውን እግድ ማንሳቱን አስታወቀ
ባለስልጣኑ እግዱ የተነሳው "ከታገዱ ድርጅቶች ጋር ባደረገው ውይይት የተፈጠረውን መግባባትና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያቀረበውን ምክረሃሳብ ከግምት በማስገባት" ነው ብሏል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ታህሳስ ወር ባወጣው መግለጫ መንግስት በድርጅቶቹ ላይ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ ጠይቆ ነበር
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስጣን ከዛሬ የካቲት 24፣2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ጥሎት የነበረውን እግድ ማንሳቱን አስታወቋል።
የሲቪል ማህበረሰብ እንቅስቃሴዎችን የመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ እግዱ የተነሳው "ከታገዱ ድርጅቶች ጋር ባደረገው ውይይት የተፈጠረውን መግባባትና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያቀረበውን ምክረሃሳብ ከግምት በማስገባት" ነው ብሏል።
በድርጅቶቹ ላይ እግዱ የተጣለው "ህግ ተላልፈው በመገኘታቸው ምክንያት" መሆኑን የጠቀሰው ባለስልጣኑ ምርመራ ካጠናቀቀ በኋላ ከድርጅቶቹ ጋር መታረም የሚገባቸው እንዲታረሙ መግባባት ላይ ተደርሷል ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ባለፈው ታህሳስ ወር ባወጣው መግለጫ መንግስት በድርጅቶቹ ላይ የጣለውን እንዲያነሳ ጠይቆ ነበር።
እግድ ተጥሎባቸው የነበሩት ድርጅቶች የመብቶችና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል፣ የህግ ባለሙያ ለሰብአዊ መብቶች፣ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጉባኤ ናቸው።
ባለስልጣኑ በድርጅቶቹ ላይ እግድ የጣለው ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆነው እየሰሩ አይደለም የሚል ምክንያት በማቅረብ ነበር። እግድ ከተጣለባቸው ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ግን ህግን በሚጻረር ተግባር እንዳልተንቀሳቀሳ በወቅቱ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።
ባለስልጣኑ እግዱን ማንሳቱን አስመልክቶ የሰጠውን መግለጫ በተመለከተ ድርጅቶች እስካሁን ያሉት ነገር የለም።