ዘለንስኪ ዩክሬን የብርቅዬ ማዕድናትን ውል ከአሜሪካ ጋር ለመፈራረም ዝግጁ ነች አሉ
የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ጠቃሚ እርምጃ ነው የተባለው ስምምነት ፕሬዝደንት ዘለንስኪና ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በመጋጨታቸው ምክንያት ሳይፈረም ቀርቷል

ፕሬዝደንት ትራምፕ አሜሪካ ለሶስት አመታት ላደረገችው ድጋፍ ዘለንስኪ "ማመስገን" እንዳለባቸው ተናግረዋል
ዘለንስኪ ዩክሬን የብርቅየ ማዕድናትን ውል ከአሜሪካ ለመፈራረም ዝግጁ ነች አሉ።
ዩክሬን ውዝግብ ያስነሳውን የብርቅየ ማዕድናት ውል ከአሜሪካ ጋር ለመፈራረም ዝግጁ መሆኗን የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል።
"ሁለቱ ወገኖች ከተስማማሙ የተዘጋጀው ስምምነት ይፈረማል" ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ የዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) ሚዲያዎች ጠቅሶ ዘግቧል።
የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ጠቃሚ እርምጃ ነው የተባለው ስምምነት ባለፈው አርብ እለት ፕሬዝደንት ዘለንስኪና ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በኃይትሀውስ ኦቫል ኦፊስ በመጋጨታቸው ምክንያት ሳይፈረም ቀርቷል።
ዘለንስኪ "የባለፈውን ለማስቀጠል የእኛ ፍላጎት ነው፤ በጎ እይታ አለን" ብለዋል።
"የማዕድን ስምምነቱን ለመፈረም ከተስማማን፣ እኛ ለመፈረም ዝግጁ ነን" ሲሉ ተደምጠዋል።
ዘለንስኪ ባለፈው አርብ እለት ወደ ዋሽንግተን ያቀኑት የዩክሬን ብርቅዬ ማዕድናትን በጋራ ለማውጣት በሚያስችለው የአሜሪካ-ዩክሬን ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ለማስቀመጥ ነበር።
የማዕድን ስምምነቱ አሜሪካ ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቅም የምታደርገው ጥረት አካል ነው።
ነገርግን ፕሬዝደንት ትራምፕ አሜሪካ ለሶስት አመታት ላደረገችው ድጋፍ ዘለንስኪ "ማመስገን" ይገባቸዋል፤ አሜሪካ ባትደግፋት ኖሮ ዩክሬን ትሸነፍ እንደነበር ተናግረዋል።
ትራምፕ አክለውም "ትስማማለህ ወይም አሜሪካ(ከሰላም ንግግር ሂደቱ) ትወጣለች" ብለዋል።"እኛ ከወጣን ብቻህን ትዋጋለህ፤ ያ ደግሞ ጥሩ ይሆናል ብዩ አላስብም።"
ፕሬዝደንት ትራምፕ ቀደም ሲል የማዕድኑን ስምሞነት "በጣም አሪፍ ስምምነት" ሲሉ አድንቀውት ነበር። ስምምነቱ አሜሪካ ለዩክሬን ባደረገችው ድጋፍ ምትክ የፋይናንስ ጠቀሜታ እንድታገኝ የሚያደርግና ጦርነቱ እንዲቅም የሚያሰችል እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።
ዘለንስኪ ባለፈው አርብ እለት ከታቀደው ጋዜጣዊ መግለጫ በፊት ከኃይትሀውስ እንዲወጡ ከተደረጉ በኋላ ስምምነቱ ሳይፈረም ቀርቷል።
ትራምፕ ግን ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ከአሜሪካ ያገኘችውን በበርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ድጋፍ በውድ ማዕድናት መክፈል እንደሚገባትና ዩክሬንም እንደተስማማች በቅርቡ ተናግረው ነበር።
ዘለንስኪ በአንጻሩ ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት አሜሪካ ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና እንድትሰጣት እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል።