በአፍሪካ ቀንድ ወሳኙን ሚና በመጫወት ላይ ያሉት ኢጋድና አፍሪካ ህብረት መሆናቸውን የኢጋድ ቃል አቀባይ ገለፁ
በአፍሪካ ቀንድ ከቀጠናዊ ውህደትና ኢኮኖሚዊ እድገት አንፃር ብዙ ለውጦች መታየታቸውን የኢጋድ ቃል አቀባይ ኑር መሃመድ ሼክ ተናግረዋል
የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ኢጋድ በፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና በሌሎች መሪዎች በኩል እየተከታተለው መሆኑን አስታውቀዋል
በአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ ያሉት የውጭ ኃይሎች ሳይሆኑ ኢጋድ እና አፍሪካ ህብረት መሆናቸውን የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የልማት ባለስልጣን /ኢጋድ/ ቃል አቀባይ ኑር መሃመድ ሼክ ተናገሩ።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ትኩረት አፍሪካ ቀንድ እየሆነ የመጣ ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆነ ሀገራት ከሌላው የአህጉሪቱ ቀጠናዎች በተለየ መልኩ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የራሳቸውን ልዩ መልእክተኞች እስከ መሾም የደርሰዋል።
አሜሪካ በቀጠናው ልዩ መልእከጣ መላኳኳ እንዲሁም ቻይና በቀጠናውe ልዩ መልእከተኛ አሰመራለሁ ማለቷ የአፍሪካ ቀንድ የጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታን በግልጽ ሚያሳይ እንደሆነም ነው የፖለቲካ ሳይንስ ልሂቃን በተለያየ ጊዜያት ሲናገሩ የሚደመጡት።
ይህንን መነሻ በማድረግ “በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለው የውጭ ኃይሎች እንቅስቃሴ የቀጠናውም ሆነ የአህጉሪቱ ተቋም ሚና የሚገድብ፣ አለፍ ብሎም በጣልቃ ገብነት ሊገለጽ የሚችል አይደለም ወይ…?” በሚል አል-ዐይን ኒውስ ለኢጋድ ቃል አቀባዩ ጥያቄ አቅርቧል።
ቃል አቀባዩ በምላሻቸው በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋሉ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም፤ ወሳኙን ሚና በመጫወት ላይ ያሉት የውጭ ኃይሎች ሳይሆኑ ኢጋድ እና አፍሪካ ህብረት ናቸው ብለዋል።
“የቀጠናው ሀገራት የኢጋድና አፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት እንደመሆናቸው የዓለም አቀፍ ተቋማት አጋዥ ሚና ከመጫወት የዘለለ ሌላ ሚና ሊኖራቸው አይችልም ሲሉም” አክለዋል።
ቃል አቀባዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው ሚና አጋዥና ገንቢ ሊሆን እንደሚገባ ጠይቀዋል።
“ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር አጋርነት እንዲኖረን እንፈልጋልን ነገር ግን በቀጠናዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ለመሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ኢጋድ እና አፍሪካ ህብረት የመሪነቱን ሚና በመጫወት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አቅም አላቸው” ሲሉም የኢጋድ ቃል አቀባዩ ኑር መሃመድ ሼክ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም፤ በአፍሪካ ቀንድ የተጋረጡ ፈተናዎች ታልፈው ብሩህ መጻኢ የሚያመላክቱ ተስፋዎች እንዳሉም ገልጸዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ከቀጠናዊ ውህደት እና ኢኮኖሚዊ እድገት አንፃር ብዙ መልካም ለውጦች መታየታቸውንም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።
ከፖለቲካ አንጻር “በሱዳን እና ሶማሊያ ያጋጠሙትን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታተ የሚያስችሉ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው” ብለዋል።
የሱዳን ሽግግርን የተሳካ ለማድረግ በሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህብራት እና መንግስት በሀገሪቱ ላለው ችግር ፓለቲካዊ መፍትሄ ለማበጀት በጠረጴዛ ዙርያ መቀመጣቸው ትልቅ እርመጃ መሆኑንም አመላክቷል።
የደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት አፈጻጸም የሚቀረው ነገር ቢኖርም በጥሩ ሁኔታ እየተሳለጠ መሆኑ፣ የሶማሊያ ፖለቲከኞች በዚህ በተያዘው ወርሃ የካቲት ምርጫ ለማድረግ መስማማታቸው ሌላው በቀጠናው እየተስተዋለ ያለ ተስፋ ሰጪ ነገር መሆኑንም አንስቷል።
“በመጪው ወርሃ ነሃሴ ምርጫ የምታደረገው ኬንያ ካሏት ጠንካራ የሚባሉ የዴሞክራሲ ተቋማት አንጻር ሰላማዊና ስኬታማ ምርጫ ታካሂዳለች የሚል እምነት አለንም ብለዋል ቃል አቀባዩ።
በኢትዮጵያ ያለውን አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተም “ኢጋድ በፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና በሌሎች መሪዎች በኩል በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እየተከታተለውና በመፍትሄዎቹ ላይ እየሰራ ነው” ሲሉ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓረቲዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የሚያሳትፈው “ብሄራዊ ውይይት”ን ለማዘጋጀት የወሰነውን ውሳኔ የሚደነቅ ነውም ብለዋል ቃል አቀባዩ።
“ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት የፖለቲካ እስረኞች መልቀቃቸውም የሚበረታታ እርማጀ ነው” ሲሉም አክለዋል።