ኢትዮጵያ የሞባይል ባንኪንግ ፈቃድ ለውጭ ኩባንያ ባለመስጠቷ ግማሽ ቢሊዮን ብር ማጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ
ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌ ብር” የተሰኘ ቀላል የተንቀሳቃሽ ስልክ መገበያያ ስርዓት ይፋ አድርጓል
ኢትዮ ቴሌኮም በሞባይል ስልክ በዓመት 3.5 ትሪሊዮን ብር ለማንቀሳቀስ ማቀዱን ገልጿል
ኢትዮጵያ የሞባይል ገንዘብ ማዛወሪራ (የሞባይል ባንኪንግ) ፈቃድ ለውጭ ኩባንያ ባለመስጠቷ ምክንያት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌ ብር የተንቀሳቃሽ ስልክ መገበያያ መተግበሪያ ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በዚሁ ምክንያት ከብዙ አገራት ተጽዕኖ እየደረሰባት ነው ብለዋል፡፡ ከተጽዕኖው ባሻገር ግማሽ ቢሊዮን ዶላር እንዳጣችም ነው የተናገሩት፡፡
የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ለውጭ ኩባንያዎች እንዳይሰጥ የተወሰነው በብሔራዊ ደህንነት ስጋት ምክንያት መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ቴሌ ብርን መጀመሩ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ ነው ሲሉም አድንቀዋል።
ቴሌ ብር በተለይም የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ላልሆኑ በገጠር አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ትልቅ እድል መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬህይት ታምሩ ናቸው፡፡
ወ/ሪት ፍሬህይት ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ 35 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው የፋይናንስ አገልግሎቶችን የሚጠቀመው ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ መልከዓምድር የቴሌኮም አገልግሎቶች ተደራሽ መሆኑን የተናገሩት ስራ አስፈጻሚዋ 53 ሚሊዮን ከሆኑት ደንበኞቹ ውስጥ 23 ሚሊዮን ያህሉ ዘመናዊ ስልኮች ተጠቃሚ ናቸውም ብለዋል።
ይህን አዲስ አገልግሎት ወደ ስራ ለማስገባት 1500 የኢትዮ ቴሌኮም ወኪሎች ስልጠና ወስደው ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ወይዘሪት ፍሬህይወት የተናገሩት።
ይህ አዲስ አሰራር በሞባይል ስልክ ገንዘብ መቀበል እና መላክ ከማስቻሉ ባለፈ የደህንነት ስጋትን እና የጊዜ ብክነትን ያስቀራልም ተብሏል።
በዚህ የግብይት ስርዓት መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም 3.5 ትሪሊዮን ብር ለማንቀሳቀስ ማቀዱንም ገልጸዋል።
በዓለማችን በየዕለቱ ከ2 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ይህ አሰራር ወደ ኢትዮጵያ ገና በመጀመር ላይ በመሆኑ የተሻለ ጥቅም እንደሚገኝበት በመድረኩ ላይ ተገልጿል።