የትግራይ ክልል የኢትዮ ቴሌኮምን የመቀሌ ጠባቂ በማባረር አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርጓል ተባለ
በ14 ቀናት ውስጥ 39 ነጥብ 8 ቢሊዮን የሳይበር ጥቃቶች ተፈጽመው እንደነበርም አስታውቋል
ለዚህም በደህንነት ካሜራዎች የተቀረጹ የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃዎች ተገኝተዋል ብሏል ኩባንያው
በትግራይ ክልል መቀሌና አካባቢው በሕግ የቴሌኮም አገልግሎት ከሚሰጠው ኢትዮ ቴሌኮም ዕውቅና ውጭ የድምጽ አገልግሎት ለማሰራት ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ተቋሙ አስታወቀ፡፡
የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ በጥቅምት መጨረሻና ህዳር መጀመሪያ ሳምንታት አካባቢ የስልክ አገልግሎትን በድምጽ ለመስጠት የሚያስችል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር ብለዋል፡፡
በክልሉ የነበረውን የቴሌኮም አገልግሎት ያቋረጠው ኩባንያው ነው በሚል ሲሰጡ የነበሩ መላ ምቶች ነበሩ፡፡ አገልግሎቱ በምን ምክንያት ሊቋረጥ እንደቻለ ሳይታወቅም ቆይቷል፡፡
ሆኖም በኩባያው የተቋረጠ ነው የሚለውን መላ ምት ያስተባበሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ምክንያቱ መታወቁን ዛሬ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል፡፡
አገልግሎቱ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መቀሌ ስራ ላይ የነበሩትን የኩባንያውን የጥበቃ ሰራተኛ በክልሉ ልዩ ኃይል እንዲባረሩ በማድረግ ነው መቋረጡንም ነው ወ/ሪት ፍሬሕይወት የገለጹት፡፡
ይህም መቀሌ ካለው የተቋሙ የደህንነት ካሜራ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ከደህንነት ካሜራው የተገኘው ተንቃሳቃሽ ምስል የትግራይ ልዩ ኃይል አባላትን ደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች የመስሪያ ቤቱን ጥበቃ በሃይል በማስወጣት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ሲያደርጉ ያሳያል፡፡ በዚህም መሰረት የክልሉ የቴሌኮም አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፡፡
አሁን ላይ በአላማጣ ከተማ የሥልክ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ መጀመሩን የገለጸው ኢትዮ ቴሌኮም በዳንሻ፣ ሁመራ፣ ማይካድራ፣ ትርካን፣ ማይጸብሪ እና ኮረም ደግሞ ከፊል አገልግሎት መስጠት እንደተጀመረ አስታውቋል፡፡
ሆኖም አገልግሎቱ በተጠቀሱት ቦታዎች በሙሉና በከፊል ቢጀምርም የመቀሌና ሽሬ ዋና ማስተላለፊያዎች መቼ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አልታወቀም፡፡ የሚጀምሩበትን ቀን በትክክል ለመናገር ይቸግራል ያሉት ወ/ሪት ፍሬህይወትም አገልግሎቱን በቶሎ ሙሉ ለሙሉ ለመጀመር የሚያስችል ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ወደ መቀሌ የሚወስዱት የቴሌኮም መስመሮች በሙሉ ተቋርጠዋል እንደ ኩባንያው ገለጻ፡፡ ሆኖም የመቀሌውም ሆነ የሽሬው ኮር ሳይቶች ውድመት አልደረሰባቸውም፡፡ የሚስተካከሉትን ለማስተካከል ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡
የመቀሌውን ኮር ሳይት በጀነሬተር እንዲሰራ ለማድረግ ጥረት እየተደረገም ይገኛል፡፡
ይህን የኮር ሳይት በህገ ወጥ መንገድ ለመጠቀም ተሞክሮ እንደነበር የገለጹት ወ/ሪት ፍሬህይወት ከፍተኛ የኮምፒውተር ጥቃት እየተፈጸመ እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡ በ14 ቀናት ውስጥ 39 ነጥብ 8 ቢሊዮን የሳይበር ጥቃቶች መፈጸማቸውንም ነው የገለጹት፡፡ ሆኖም ሀገር አቀፉን የቴሌኮም ስርጭት ለማቋረጥ በማሰብ የተፈጸሙትን እነዚህን ጥቃቶች ለማክሸፍ ተችሏል፡፡
ሙከራዎቹ በሃገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የፋይናንስ፣ የትምህርት፣ የብሮድካስት እና ሌሎችንም ስርዓቶች ለማናጋት በማሰብ ጭምር የተፈጸሙ ነበሩም ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፡፡