በጃፓን ያገቡ ሴቶች ጵንስ ለማቋረጥ የባላቸውን ፍቃድ ለማግኘት እንደሚገደዱ ይውቃሉ?
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 800 ሺህ ብቻ ህጻናት የተወለዱባት ቶኪዮ፥ የህዝብ ቁጥሯ መቀነሱ አሳእቧታል
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳም “እንደ ማህበረሰብ የመቀጠላችን ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል” ብለዋል።
በጃፓን የውልደት መጠን እያሽቆለቆለ መሄድ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነገረ።
በፈረንጆቹ 2022 ዓመት 800 ሺህ ብቻ ህጻናት የተወለዱባት ቶኪዮ፥ የህዝብ ቁጥሯ ካላፈው አመት በ0 ነጥብ 43 በመቶ ቀንሶባታል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ “እንደ ማህበረሰብ የመቀጠላችን ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል” ነው ያሉት።
“እያረጀች ባለችው ሀገር” የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እየቀነሰ፥ እድሜያቸው የገፉትም ህይወታቸው እያለፈ የህዝብ ቁጥሯ በየአመቱ ማሽቆልቆሉን ተያይዞታል።
ይህን ለመግታትም “ጊዜው አሁን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህጻናትን ለተመለከቱ ጉዳዮች መንግስት የሚያወጣውን ወጪ በእጥፍ ሊያሳድግ ይገባል፤ ልዩ ፖሊሲዎችን መቅረጽም ያስፈልጋል ብለዋል።
በቀጣይ ሚያዚያ ወርም አሳሳቢ የሆነውን ጉዳይ የሚከታተል አዲስ ተቋም በይፋ ስራ እንደሚጀምርም ገልጸዋል።
በአለማችን ረጅም በህይወት የመቆያ እድሜ በሚመዘገብባት ጃፓን፥ ከ1 ሺህ 500 ሰዎች አንዱ 100 እና ከዚያ በላይ አመት እድሜ ይኖረዋል።
እድሜያቸው ከ65 አመት በላይ የሆነ ጃፓናውያን ቁጥርም ከ36 ሚሊየን በላይ ነው፤ ይህም ከጠቅላላው ህዝብ 30 በመቶውን ይሸፍናል።
ረጅም የስራ ጊዜ፣ የኑሮ ውድነት፣ ለህጻናት እንክብካቤ የማይመቹ ሁኔታዎች የጃፓናውያንን የመውለድ ፍላጎት መገደባቸው ይነገራል።
መንግስት የውልደት መጠኑን ከፍ ለማድረግ ለሚወልዱ ጥንዶች ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን የሚጠቅሰው የሲ ኤን ኤን ዘገባ፥ ይሁን እንጂ ባላፉት አመታት የሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር ቀነስ እንጂ አልጨመረም ብሏል።
ቶኪዮ መውለድን ለማበረታታት ከወሰደቻቸው እርምጃዎች መካከል ያገቡ ሴቶች ከባላቸው ይሁንታ ውጪ ጽንስ ማስወረድ አይቻልም የሚለው አንዱ ነው።
ነገር ግን የተደፈሩ ሴቶች እና ጽንሱ የሴቷን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታን የሚያስከትል ከሆነ ጽንሱ እንዲቋረጥ ትፈቅዳለች ይላል የኢንዲፐንደንት ዘገባ።
ቶኪዮ ይህን መሰሉን ክልከላ ካስቀመጡ ከበለጸጉት አንዷ መሆኗን የሚያነሱ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አቋሟን እንድስታስተካክል እያሳሰቡ ነው።
የወሊድ መቆጣጠሪያን መውሰድን እንደ አውሮፓውያኑ በ1999 የፈቀድችው ሀገር ከቡድን 7 አባል ሀገራት ለጾታ እኩልነት ቦታ በመሰጠት ከግርጌ ያስቀምጧታል።
ጃፓንን ጨምሮ የእስያ ሀገራት ግን መውለድን ለማበረታታን የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ገጥመዋቸዋል።
ደቡብ ኮሪያ በቅርቡ የአለማችን ዝቅተኛውን የውልደት ምጣኔ (አንዲት ሴት በህይወት ዘመኗ በአማካይ የምታገኘው ልጅ 0 ነጥብ 79 ነው) ማስመዝገቧ ይታወሳል።
ቻይናም ከፈረንጆቹ 1960 ወዲህ የህዝብ ቁጥሯ መቀነሱን ይፋ ማድረጓ አይዘነጋም።