ውሳኔው ታሊባን ወደ ስልጣን ከተመለሰ በኋላ የሴቶችን ትምህርት የሚገድብ የቅርብ ጊዜው ፖሊሲ ነው ተብሏል
በአፍጋኒስታን ታሊባን ሴቶች ዩኒቨርሲቲ እንዳይገቡ መከልከሉን በመቃወም በካቡል በተካሄደው ተቃውሞ ላይ ሴቶችን እያሰረ ነው፡፡
አስካሁን በተቃውሞው የተሳተፉ አምስት ሴቶችና ሶስት ጋዜጠኞች እንዳሰረም ነው የተገለጸው፡፡
የታሊባን ውሳኔ ያስቆጣቸው ሴቶች ከአፍጋኒስታን መዲና ካቡል በተጨማሪ በታክሃር ግዛት የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄድ ላይ ናቸውም ተብሏል፡፡
ታሊባን የሴቶችን የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ እንዲታገድ ያዘዘው ተማሪዎች ለፈተና ዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት በመሆኑ፤ በርካታ ተማሪዎች በውሳኔው መበሳጨታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
አፍጋኒስታንን ከሁለት አስርት በኋላ ዳግም እያሰተዳደረ የሚገኘው ታሊባን ሴቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዳይገቡ ያገደበት የማክሰኞ ውሳኔን ተከትሎ ፤ የጸጥታ ኃይሎች እገዳው ከታወጀ ከአንድ ቀን በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይገቡ ሲከልክሉም ታይተዋል፡፡
ውሳኔው ታሊባን ወደ ስልጣን ከተመለሰ በኋላ የሴቶችን ትምህርት የሚገድብ የቅርብ ጊዜው ፖሊሲ ነው ተብሏል።
የአፍጋን ልጃገረዶች ቀድሞውንም ቢሆን ከአብዛኞቹ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተገለሉ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
የታሊባን አስተዳደር የትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አገዳው በምሁራን አስፈላጊ የዩኒቨርሲቲውን ስርዓተ ትምህርት ከገመገሙ በኋላ የተወሰነ መሆኑን ገልጾ ተስማሚ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ሴቶች ሴቶች ዩኒቨርሲቲ መግባት አይችሉም ብሏል፡፡
በኋላም የታሊባን የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ነዳ መሀመድ ናዲም ፤ “ሴቶች የአለባበስ ስርዓትን ባለማከናወናቸው ከዩኒቨርስቲ ታግደዋል” ሲሉ በሀገሪቱ ቴሌቭዢን ጣቢያ ተናግረዋል፡፡
ታሊባን በመስከረም ወር 2021 የአሜሪካ መራሹ ጦር አፍጋኒስታንን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ በትረ ስልጣንን በድጋሚ መጨበጡ ይታወሳል፡፡
መንግስት ሆኖ ሀገር እየመራ ያለው ታሊባን በሴቶች መብት ላይ ማሻሻያ ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም፤ ሴቶች በፓርኮች እና የስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዳይገኙ የሚያስገድድ መመሪያ ሲያወጣ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡