ኢትዮጵያ በ2023 የዓለም ደስታ ሪፖርት ላይ በስንተኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች?
በዓለም የደስታ ሪፖርት ፊንላንድ ዘንድሮም ቀዳሚ ስትሆን ሞሪሺየስ ደግሞ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ተብላለች
አፍጋኒስታን እና ሊባኖስ ደግሞ ደስታ የራቃቸው ሀገራት በሚል ተቀምጠዋል
ኢትዮጵያ በ2023 የዓለም ደስታ ሪፖርት ላይ በስንተኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች?
የዓለም ደስታ ሪፖርት የአሜሪካው ኮሎምቢያ ዩንቨርሲቲ እና የብሪታንያው ለንደን የኢኮኖሚክስ ዩንቨርሰቲ ከዘላቂ ልማት ኔትወርክ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም ጋር በመቀናጀት በየዓመቱ ይፋ ያደርጉታል፡፡
እነዚህ ተቋማትም እየተጠናቀቀ ያለው የ2023 ዓመት የሀገራትን የደስታ ሪፖርት ይፋ አድርገዋል፡፡
ተቋማቱ የሀገራትን ደስታ የለኩት የዜጎች ዓመታዊ ገቢ፣ የጤና እና ማህበራዊ አገልግሎት መጠን፣ የሙስና ደረጃ እና የዜጎች በነጻነት የመወሰን መብትን እንደ መስፈርት መጠቀማቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሪፖርት መሰረት ፊንላንድ፣ ዴንማርክ፣ አይስላንድ እስራኤል፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድ፣ ሉግዘምበርግ እና ኒውዝላንድ ከ1ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀይላ የሆነችው አሜሪካ 15ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ቻይና 64ኛ እንዲሁም የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን ደግሞ ከአምናው በአንድ ደረጃ አሽቆልቁላ በ16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ከአፍሪካ በደስታ ብዛት አንደኛ የሆነችው ሞሪሺየስ ከዓለም ደግሞ 59ኛ ስትገኝ አልጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ ሁለተኛ እና 3ኛ ደረጃዎች ላይ የተቀመጡ ሀገራት ናቸው፡፡
ደስተኛ ህዝብ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት እነማን ናቸው?
ጉረቤት ሀገር ኬንያ ከምስረቅ አፍሪካ አንደኛ ስትሆን ከዓለም በ111 ደረጃ ላይ ስትገኝ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ስምንት ደረጃዎችን አሻሽላለች፡፡
ኢትዮጵያ በዘንድሮው ውድድር ላይ ከተሳተፉ 137 ሀገራት መካከል በ124ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ሰባት ደረጃዎችን እንዳሻሻለች ተገልጿል፡፡
በ2022 በዚህ ሪፖርት ተካተው የነበሩ ዘጠኝ የዓለማችን ሀገራት ዘንድሮ አልተካተቱም የተባለ ሲሆን ብዙ ሀገራት ደረጃቸውን ያሻሻሉት በዚህ ምክንት ሊሆን እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡
137 ሀገራት በተካተቱበት በዚህ ሪፖርት አፍጋኒስታን የመጨረሻውን ደረጃ ስትይዝ ሊባኖስ እና ሴራሊዮን 136 እና 135ኛ ደረጃዎችን በመያዝ ደስታ የራቃቸው ሀገራት ተብለዋል፡፡