ፊንላንድ ለስድስት ተከታታይ አመት የአለማችን ደስተኛ ሀገር ተብላ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛለች
በአለማችን ደስታ የሞላባቸውና ደስታ የራቃቸው ሀገራት ደረጃ ይፋ ሲደረግ ፊንላንድን አሁንም የሚደርስባት አልተገኘም።
ገለልተኛ ቡድን የሚያጠናውና ከ150 በላይ ሀገራትን የደስተኝነት ደረጃ የሚዳስሰው ሪፖርት በፈረንጆቹ መጋቢት 20 ታስቦ ከሚውለው “የአለም የደስተኝነት ቀን” ጋር ተያይዞ ይፋ ተደርጓል።
የማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ ጤና፣ ነጻነት፣ ለጋስነት እና ከሙስና መጽዳት የሚሉ ስድስት መስፈርቶችም ደረጃውን ለማውጣት ውለዋል።
በእነዚህ መስፈርቶች ለ150 ሀገራት ከ10 በተሰጠ ነጥብ ደረጃው የወጣ ሲሆን፥ ደስተኛ የተባሉት እንደ ፊንላንድ ያሉ ሀገራት 7 ነጥብ 32 ሲያስመዘግቡ፥ ደስታ የራቃቸው እንደ አፍጋኒስታን ያሉት ደግሞ 1 ነጥብ 67 ነጥብ አግኝተዋል።
በዚህም መሰረት ባለፉት ስድስት ተከታታይ አመታት ቀዳሚዋ ደስተኛ ሀገር የተሰኘችው ፊንላንድ በ2023ትም የአለማችን በደስታ የተሞላች ሀገር ሆና ተመርጣለች ይላል ሪፖርቱ።
ፊንላንድ ለዜጎቿ የምትሰጠው የላቀ የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ለበርካታ ዜጎች የደስታ ምንጭ መሆኑን የአልቶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ጠቅሶ ፎርብስ ዘግቧል።
ስራ የሌላቸው ሰዎች የሚያገኙት የድጎማ ገንዘብ እና ነጻ የጤና አገልግሎትም በፊንላንድ ደስታ የራቃቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል ተብሏል።
የኖርዲክ ሀገራት የደስተኝነት ደረጃ በኮሮና ቫይረስ ወቅት እንኳን ብዙም ለውጥ አለማሳየቱን ያነሳው ሪፖርቱ፥ በሀገራቱ የበጎነት ወይም ቸርነት ምጣኔው በ25 በመቶ እድገት ማሳየቱን አመላክቷል።
ዴንማርክ እና አይስላንድ መሪዋን ፊንላንድ ተከትለው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን፥ እስራኤል ባለፈው አመት ከነበረችበት 9ኛ ደረጃ ወደ 4ኛ ከፍ ብላለች። አሜሪካ እና ብሪታንያ ደግሞ 15ኛ እና 19ኛ ደረጃን መያዛቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።
የ2023 10ሩ የአለማችን ደስተኛ ሀገራት
1. ፊንላንድ
2. ዴንማርክ
3. አይስላንድ
4. እስራኤል
5. ኔዘርላንድስ
6. ስዊድን
7. ኖርዌይ
8. ስዊዘርላንድ
9. ሉግዘንበርግ
10. ኒውዝላንድ
ጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬንም ደረጃው ዝቅ ብሎ 70ኛ እና 92ኛ ተቀምጠዋል።
ሪፖርቱ በአለማችን ደስታ የራቃቸውን 20 ሀገራትም ይፋ አድርጓል።
እስከ 10ኛ ከተዘረዘሩት ሀገራት ውስጥ ስምንቱ በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ህንድና ላይቤሪያን ተከትላ 14ኛ ደረጃን ይዛለች፤ ግብጽ ደግሞ 17ኛ ላይ ተቀምጣለች።
አስሩ ደስታ የራቃቸው የአለማችን ሀገራት
1. አፍጋኒስታን
2. ሊባኖስ
3. ሴራሊዮን
4. ዚምባቡዌ
5. ኮንጎ
6. ቦትስዋና
7. ማላዊ
8. ኮሞሮስ
9. ታንዛኒያ
10. ዛምቢያ