የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ ተባለ
ኢትዮጵያን ለቀጣይ 5 ዓመታት የሚመራው አዲስ መንግስት ነገ በይፋ የሚመሰረት መሆኑ የሚታወቅ ነው
የብልጽግና ፓርቲ ነገ ጠ/ሚ/ር ዐቢይን ለቀጣዮቹ ዓመታት መንግስትን እንዲመሩ በዕጩነት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሀሙዱ ቡሀሪ ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የፕሬዝዳንቱ ሚዲያና የሕዝብ አማካሪ አስታወቁ፡፡
አማካሪው ፌሚ አዴሲና፤ ፕሬዝዳንት ቡሃሪ በኢትዮጵያ ነገ አዲስ መንግስት ለመመስረት በሚደረገው መርሃ ግብር ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በስነ ስርአቱ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ የወጣው መርሃ ግብር እንደሚያመለክትም ነው አማካሪው የተናገሩት፡፡
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ቅርጽ ፕሬዝዳንታዊ አይሆንም- ቢቂላ ሁሪሳ
ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሚጠበቁት የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት የደህንነት ኃላፊያቸውን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣኖቻቸውንም ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሏል፡፡ ከፕሬዝዳንት ቡሃሪ ጋር የደህንነት ሃላፊያቸው አምባሳደር አህመድ ራፋይ አቡባክር አዲስ አበባ እንደሚገቡ አማካሪው ገልጸዋል፡፡
የናይጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆፍሪ ኦኒያማ ትናንትና ምሽት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ የናይጀሪያ ባለስልጣናቱ በኢትዮጵያ እስከ ማክስኞ እንደሚቆዩ ይጠበቃል፡፡
በመንግስት ምስረታ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ከማድረግም ባለፈ ከሌሎች ሀገራት እና መንግስታት መሪዎች ጋር በሚዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን ለቀጣይ 5 ዓመታት የሚመራው አዲስ መንግስት ነገ በይፋ የሚመሰረት መሆኑ ይታወቃል፡፡ አዲሱ መንግስት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ባሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ የሚመሰረት ነው፡፡
ብልጽግና በምርጫው ካሸነፈ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ ውክልና እንዲኖራው ያደርጋል-ጠ/ሚ ዐቢይ
ብልጽግና፤ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ጎማ ወረዳ በሻሻ ተወዳድረው ያሸነፉትን ፕሬዝዳንቱን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ቀጣዩ የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ለሹመት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሀገሪቱ መንግስት መሪ ሆነው እንደሚሰየሙ በሚጠበቅበት በዚህ መርሃ ግብር ላይ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የናይጄሪያውን ፕሬዝዳንት መሃመዱ ቡሃሪን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡