የመንግስት ምስረታ መርሃ ግብሩን ለመታደም እንግዶች ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ነው
ኢትዮጵያ ነገ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ/ም አዲስ መንግስት ትመሰርታለች፡፡
አዲሱ መንግስት 6ኛውን ሃገር አቀፍ ምርጫ በአብላጫ ባሸነፈው ውህድ ፓርቲ ብልጽግና የሚመሰረት ነው፡፡
ከነገው የመንግስት ምስረታ መርሃ ግብር ጋር በተያያዘ ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑት የአዲስ አበባ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
ብልጽግና ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ/ም የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ በማግኘት ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ቦርዱ ምርጫውን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው ውጤት መሰረት ብልጽግና ፓርቲ ምርጫ ከተደረገባቸው 436 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ 410ሩን አግኝቷል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሰል ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎችም መቀመጫዎችን አግኝተዋል፡፡
በወቅቱ ብልጽግና በምርጫው ካሸነፈ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ ውክልና እንዲኖራቸው ያደርጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታውቀው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ ብልጽግና አዲስ አበባን ጨምሮ ባሸነፈባቸው የተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች አስተዳደሮችን ሲያቋቁም የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን አካቷል፡፡
ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በአዲሱ የአማራ ክልል ም/ቤት ተሾሙ
ነገ በሚመሰረተው አዲስ መንግስት ውስጥ ለተለያዩ ሹመቶች የሚታጩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እንደሚኖሩም ይጠበቃል፡፡
በነገው መርሃ ግብር ለመሳተፍ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች እና እንግዶች ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ነው፡፡
እንግዶቿን ለመቀበል ሽርጉድ ላይ ያለችው አዲስ አበባም የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ባንዲራዎችን በዋና ጎዳናዎቿ እያውለበለበች ትገኛለች፡፡
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሀሙዱ ቡሀሪ የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ሚኒስትሮቻቸውን ይዘው ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ መጀመራቸውን የፕሬዝዳንቱን የሚዲያና የሕዝብ አማካሪ ዋቢ አድርጎ አል ዐይን አማርኛ ከሰዓታት በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡