በስቀለት ማግስት የሚውለው ቅዳሜ /ቀዳም ሰዑር/ ስያሜዎች…
የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም “ቀዳም ስዑር ወይም የተሻረች ቅዳሜ” ተብላለች
በዚች ዕለች ከድሮው በተለየ መልኩ ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ በጾም በማሰብ ይውላሉ
በስቅለት እለት ማግስት እና የትንሳዔ በዓል ዋዜማ ላይ የምትገኘው ቅዳሜ ከወትሮ በተለየ “ቀዳም ስዑር ወይም የተሻረች ቅዳሜ” ተብላለች።
በየዓመቱ በትንሣኤ ዋዜማ የሚለውለው "በቀዳም ስዑር" የሚከበረው የገብረ ሰላመ በዓል በዛሬው እለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓተ አምልኮ ተከብሯል
በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን መፈጸሙ የሚዘከርበት፣ በመስቀል ላይም በፈጸመው የማዳን ሥራ ለዓለም ድኅነትን መስጠቱ የሚታወጅበት ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ነው።
በበዓሉ ላይ በአዳም በደል ምክንያት በሰው ልጆች የውድቀት ዘመን ማብቃቱ የሚታወጅበት ቄጤማም በቅዱስ ፓትርያርኩ ለበዓሉ ታዳሚዎች ሁሉ ከመልካም ምኞት ጋር መታደሉን ከማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በስቅለት እለት ማግስት እና የትንሳዔ በዓል ዋዜማ ላይ የምትገኘው ቅዳሜ “ቀዳም ሥዑር” በእምነቱ ተከታዮች ዘንድም የተለያዩ ስያሜዎች እንዳላትም ይነገራል
ቀዳም ሰዑር ስያሜዎች እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ቀዳም ሥዑር
በሰሙነ ሕማማት በስቀለት ማግስት የሚውለው ቅዳሜ ቀዳም ሥዑር በመባል ይጠራል። በዚህ ዕለት ከድሮው በተለየ መልኩ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹን ከዲያብሎስ አገዛዝና እስራት ነጻ ለማውጣት የተቀበለውን መከራ፣ እንዲሁም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ማደሩን በማሰብ በጾም ታስቦ ስለሚውል ቀዳም ስዑር ወይም የተሻረው ቅዳሜ ተብሏል። የማይጾመው ቅዳሜ ስለሚጾም ስዑር /የተሻረ/ ተብሏል።
ለምለም ቅዳሜ፡-
ካህናቱ ሌሊት ለምእመናን ለምለም ቄጤማ ስለሚያድሉ ዕለቲቱ በዚህ ስያሜ ተሰይሟል። ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።
በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ” የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ።
ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ። ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ። ይህም አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው።
ቅዱስ ቅዳሜ
ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ነው። በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል።
በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ መባሉን የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።