ዋግነር ቅጥረኛ ቡድን ለኦርቶዶክስ የፋሲካ በዓል እስረኞችን ወደ ዩክሬን ኃይሎች መላኩን አሳውቋል
ከ100 በላይ የዩክሬን የጦር እስረኞች ለፋሲካ በዓል ተለቀቁ።
የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደር ቡድን ዋግነር፤ የፋሲካን በዓል ለማክበር ቢያንስ 100 የዩክሬን የጦር እስረኞችን ወደ ዩክሬን ኃይሎች መላኩን አሳውቋል።
የቡድኑ መስራች ዮቪጄንሲ ፒሪጎዚን በቴሌግራም በተለጠፈ ተንቀሳቃሽ ምስል "ሁሉንም አዘጋጁ፣ አብሏቸው፤ አጠጧቸው፣ የቆሰሉትን ተከታተሉ" ሲሉ ተደምጠዋል።
በምስሉ የእስረኞች ቡድን የኦርቶዶክስ ፋሲካ በዓልን ለማክበር ወደ ዩክሬን ኃይሎች እንደሚመለሱ ሲነገራቸው ታይቷል።
እስረኞቹ ከፊሉ ሲያነክሱ አንዳንዶቹም ጓዶቻቸው በቃሬዛ ተሸክመዋቸው ጭቃማ በሆነ መንገድ ላይ ሲሰለፉ መታየታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጽ/ቤት ኃላፊ አንድሪይ ያርማክ 130 የዩክሬን የጦር እስረኞች "በታላቁ የትንሳኤ ልውውጥ" ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም ኃላፊው ምን ያህል ሩሲያዊያን እንደተመለሱ ግልጽ አላደረጉም።
የሩሲያው ዋግነር ግሩፕ የዩክሬይንን ጦር በምስራቅ ግንባር ከባክሙት ቀስ በቀስ እያባረረ ነው ተብሏል።
ዋግነር አብዛኛውን ከተማዋን መቆጣጠሩን ተናግሯል። ምንም እንኳን የዩክሬን ኃይሎች ማፈግፈጋቸውን ደጋግመው ቢቃወሙም።