ሶስቱ ሀገራት በ"አፍሪካዊ መፍትሔ"ላይ ተስማምተዋል
በግድቡ ድርድር ላይ ግብጽ ተመድ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቃ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን አልተስማማችም
ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ የአፍሪካ ህብረት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተስማምተዋል
ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ የአፍሪካ ህብረት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተስማምተዋል
ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን በትናንትናው እለት በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ መሪነት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ወይይቱ በአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት የመሪዎች ቢሮ የገጽ ለገጽ (የኦንላይን) የተካሄደ ሲሆን የሶስቱም ሀገራት መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሣ ፋኪ ማሃማትም በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡
በውይይቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለተመለከቱ የልዩነት ጉዳዮች በህብረቱ መሪነት አፍሪካዊ እልባትን ለመስጠት ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ኢትዮጵያ ወትሮውኑ አስጠንክራ ስትናገር የነበረው ይህ የመፍትሄ ሃሳብም በግብፅና ሱዳን በኩል ተቀባይነትን አግኝቷል።
ግብጽ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በግድቡ ድርድር ላይ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቃ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን እንደማትስማማ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡ በግብጽ ጥያቄ መሰረት አሜሪካና የአለም ባንክ የተሳተፉበት ሶስቱ ሀገራት በዋሽንግተን ያካሄዱት ድርድር ያለስምምነት ከተቋጨ ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ጉዳዮን ቢያየው የሚል ሀሳብ ሲነሳ ነበር፡፡
የዋሽንግተኑ ድርድር የቋረጠው ኢትዮጵያ ሀገራዊ ውይይት ማድረግ ያስፈልገኛል በማለቷና ወደ ዋሽንግተን በለመሄዷ ነበር፡፡
አንዳንድ የግብፅ እና ምዕራባዊ ብዙሃን መገናኛዎች ሙሌቱ ያለስምምነት እንዳይፈጸም እና በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት የግድቡ የቴክኒክ ውይይቶች እንዲቀጥሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ነገርግን ኢትዮጵያ ዛሬ ጠዋት ባወጣችው መግለጫ “በቀጣዮቹ 2 ሳምንታት የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት እንደምትጀምር” አስታወቀች፡፡ መግለጫው ሶስት ሀገራት በግድቡ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥለው ሁለት ሳምንታት እንዲጠናቀቅ ተስማምተዋል፡፡
ቀደም ብላ ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ ተደረሰም አልተደረሰም ሙሌቱ በተያዘለት ጊዜ ይፈጸማል በሚል ደጋግማ ማስታወቋ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ግድቡ ለልማት የሚውል ፕሮጀክት መሆኑንና በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት የጎላ ጉዳት እንደማያደርስ እየገለጸች ሲሆን በአንጻሩ ግብጽ ከናይል የምታገኘው የውሃ መጠን “ይቀንስብኛል” በማለት ቅሬታ ስታሰማ ቆይታለች፡፡
ግብጽና ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ የገቡ ሲሆን ሱዳን በአንጻሩ መሀል ላይ ለመሆን እየሞከረች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በድርድሩ ስምምነት ላይ ተደረሰም ፣ አልተደረሰ በመጪው ሀምሌ ወር የግድቡን የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ከመጀመር እቅዷ ፈቅ እንደማትል እየገለጸች ነው፡፡ የኢትዮጵያን የውኃ ሙሌት እቅድ ግብጽና ሱዳን አይቀበሉትም፤ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የዉኃ ሙሌት እቅድን አንቀበልም ብለዋል፡፡