5ኛው የዓለም የሌዘር ጉባዔ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው
ኢትዮጵያ ትልቅ የሌዘር ከተማ ለመገንባት እየሰራች መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህ የተገለጸው በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 5ኛው የዓለም የሌዘር ጉባዔ ላይ በተሰጠው መግለጫ ነው።
በመግለጫው ላይ የተገነኙት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተካ ገብረኢየሱስ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ግዙፍ የሆነ የቆዳ (ሌዘር) ከተማ ልትገነባ በሂደት ላይ መሆኗን አንስተዋል።
የቆዳ ከተማው በሞጆ የሚገነባ መሆኑን ያነሱት አቶ ተካ፤ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ፋብሪካዎች አንድ ቦታ የሚይዝ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በከተማው ውስጥም ቆዳ ከሚያለፉ ጀመሮ የምርት ሂደቱ ተጠናቆ ለገበያ የሚያቀርቡ እና ጫማ እና ሌሎች የቆዳ ውጤቶች ፋብሪካዎች እንደሚገቡም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም የቆዳ አምራቾች በጋራ የሚጠቀሙበት ግዙፍ የጋራ ፍሳሽ ማስወገጃ እና ማጣሪያ እንደሚኖረውም አቶ ተካ አስታውቀዋል።
የቆዳ ከተማ ግንበታውም በመንግሰት፣ በግል እና በዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች ትብብር የሚሰራ መሆኑንም አቶ ተካ አስታውቀዋል።
“ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ጥሬ ቆዳ ብቻ ለውጭ ገበያ ታቀርብ ነበር፤ አሁን ላይ ግን ጥራታቸውን የጠበቁ ቆዳ ምርቶችን ለገበያ እያቀረበች ነው” ያሉት አቶ ተካ፤ ቆዳ ከተማው ይህንን የበለጠ ያሳድገዋልም ብለዋል።
5ኛው የዓለም የሌዘር ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄዱም ለዚህ የቆዳ ከተማ መሳካት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም አንስተዋል።
የተባሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ተወካይ ኡሌራ ክላብሮ በበኩላቸው፤ ዩኒዶ ለኢንዱስትሪ ከተማው እውን መሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
በተለይም ምቹ የሆነ የሌዘር ከተማ እንዲፈጠር እና የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የጋራ ፍሳሽ ማስወገጃ እና ማጣሪያ ፐሮጀክቱ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ሞጆ ከተማ የኢትዮ-ጅቡቲ መንገድ ላይ የምትገኝ መሆኗ እና ከኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር የሚያገኛት እንደመሆኑ ለሌዘር ከተማ ግንባታው ተመራጭ እንዳደረጋትም አስታውቀዋል።
የኢትዮጰያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ሰይድ በበኩላቸው፤ በሞጆ የሚገነባው የቆዳ ከተማ ከቆዳ አምራቾች በተጨማሪ ለቆዳ ምርት የሚያገለግሉ የኬሚካል ፋብሪካዎችን ጨምሮ ሌሎች የቆዳ ምርት ግብዓት ፋብሪካዎችን በውስጡ የያዘ ነው።
የሞጆ የቆዳ ከተማ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ አሁን ላይ ወደ ግንባታ ሂደት እየተገባ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በመግለጫው ላይ በማከልም 5ኛው የዓለም የሌዘር ጉባዔ እኛ 36ኛውን ዓለም አቀፍ የሌዘር ቴክኖሎጂ እና ኬሚስቶች ህብረት ጉባዔ ከጥቅምት 22 እስከ 26 2014 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ጉባዔ ላይ ከ20 ሀገራት የተውጣጡ 250 ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች፣ አምራቾች፣ ኢንቨስተሮች እና በፋሽኑ ዘርፍ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚሳተፉ ተነግሯል።
በተጨማሪም የ2021 የአፍሪካ ሶርሲንግ የፋሽን ሳምንት እና የቆዳ ምርቶች የንግድ ትርኢት ከህዳር 24 እስከ ህዳር 27 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም ታውቋል።
በፋሽን ሳምንቱ ላይም ከ25 ሀገራት የተውጣጡ ከ250 በላይ አምራቾች እና ሻጮች ይሳተፉበታል የተባለ ሲሆን፤ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል ብለዋል አዘጋጆቹ።