ኢትዮጵያ በአረብ ሊግ ላይ ያላትን ቅሬታ በኢትዮጵያ ለሚገኙት የአልጀሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጸች
ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ በግድቡ ዙሪያ ለግብፅ እና ሱዳን ያደላ አቋም ማራመዱን ለአልጄሪያ ገልጻለች
አልጄሪያ የአረብ ሊግ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያራመደውን አቋም ለማስተካከል ጥረት አደራጋለሁ ማለቷም ተገልጿል
የአረብ ሊግ በሕዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ ላይ ተገቢ ያልሆነ፤ ለግብፅ እና ለሱዳን ብቻ ያደላ አቋም ማራመዱን በጉብኝት ላይ ለሚገኙት የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወቀሰች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ ከፕሬዝዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸውም ኢትዮጵያ፤ የዐረብ ሊግ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያራመደውን አቋም እንዲያስተካክል ለአልጀሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማስረዳቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትር ላማምራ በሕዳሴ ግድብ፣ በኢትዮ ሱዳን ድንበር፤ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል ነው የተባለው፡፡ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የዐረብ ሊግ አባል ሀገራት በኳታር ዶሃ አድርገውት በነበረ ስብሰሳ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ጣልቃ እንዲገባ ባወጡት መግለጫ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በዐረብ ሊግ አባል ሀገራት የወጣውን መግለጫ ወድቅ ከማድረግም ባለፈ፤ ሊጉ የተሳሳተ ውሳኔ ሲያሳልፍ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ፤ ይህም ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ ላይ ለሚያነሱት መሰረተ ቢስ ጥያቄ ያለውን ድጋፍ ለማመላከት የተደረገ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያም ቅሬታዋን የአረብ ሊግ አባል ሀገር ለሆነችው አልጀሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ መግለጿን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል፡፡ ዐረብ ሊግ ለአንድ ወገን ብቻ ያደላ አቋም ከማራመዱም በላይ አቋሙ፤ በኢትዮጵ ኪሳራ ላይ የተደረገ እንደሆነ ለአልጀሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደተብራራላቸው ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ፤ የዐረብ ሊግ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘውን የተሳሳተ ያሉትን አቋም እንዲያስተካክል አልጄሪያ የበኩሏን ሚና እንድትጫወት መጠየቋን አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል፡፡
የአልጀሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ በበኩላቸው ሀገራቸው የዐረብ ሊግ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያራመደውን አቋም ለማስተካከል ጥረት እንደምታደርግ መግለጻቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አልጀሪያ በረራ እንዲያደርግም አልጀሪያ ጠይቃለች ተብሏል፡፡