ሸበሌ የተባለች የኢትዮጵያ መርከብ ከህንድ የጫነችውን ስኳርና ሩዝ ይዛ በርበራ ወደብ የደረሰቸውው
ሸበሌ የተባለች የኢትዮጵያ መርከብ ከ11ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ስኳርና ሩዝ ይዛ በርበራ ወደብ መድረሷን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት፤ መርከቧ ከህንድ የጫነችውን ስኳርና ሩዝ ይዛ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ድርሻ ባላት የበርበራ ወደበ እያራገፈች ነው።
በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ የኢትዮጵያ መርከቦች ወደ በርበራ ወደብ ጉዞ ሲያደርጉ ከ 20 ዓመታት በኋላ ሸበሌ መርከብ ሁለተኛ ናት።
ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ከ20 ዓመታት በኋላ ጊቤ መርከብ በበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ጉዞ አድርጋ ነበር፤ በዚህ ጉዞም 11 ሺህ 200 ሜትሪክ ቶን የፍጆታ ዕቃ ለሶማሌላንድ ገበያ ማጓጓዟ ይታወሳል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት አድማስ የተባለች ሁለገብ ጭነት ጫኝ መርከብ እንዲሁም አዋሽ የተባለቸው የነዳጅ ጫኝ መርከብ ወደ በርበራ ወደብ ጉዞ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በበርበራ ወደብ የተጀመረው አገልግሎት የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጿል።
ከዚህ ባለፈም የሱማሌላንድ ነጋዴዎች ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን የገለጸው ድርጅቱ፤ አገልግሎት መስጠቱን በመደበኛነት እንደሚቀጥል ገልጿል።
ጊቤና ሸበሌ የተባሉት መርከቦች በኮሪደሩ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ መሆናቸውንም የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገልጿል።
በነሐሴ ወር አጋማሽ ጊቤ መርከብ 15ሺ ሜትሪክ ቶን ሩዝ በመጫን በርበራ ወደብ እንደምትገባ ድርጅቱ ገልጿል፡፡
በበርበራ ወደብ፤ ዲ ፒ ወርልድ 51 በመቶ፣ ሶማሌላንድ 30 በመቶ እና ኢትዮጵያ ደግሞ 19 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው መገለጹ ይታወሳል።