ኢትዮጵያ በርበራን መጠቀም መጀመሯ ንግዱ እንዲፋጣንና አላስፈላጊ ወጪዎች እንዲቀንሱ ያደርጋል
የኤርትራን ነጻ ሀገርነት ተከትሎ ኢትዮጵያ የምፅዋንም የአሰብንም ወደቦች መጠቀም በማቆሟ፤ ሀገሪቱ ከቀይ ባህር ጋር ተራርቃ ቆይታለች።
ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችና ወደ ባሕር መተንፈስ ያልቻለች ሀገር ከሆነች 30 ዓመታት ተቆጥረዋል።
ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ከወጪና ገቢ ዕቃዎቿን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው በቀጥታ በጅቡቲ በኩል ስታስገባ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ዕቃዎቿን ከጅቡቲ ወደብ በተጨማሪም በሌሎች በሌሎች ወደቦች እንድታስገባ ተጨማሪ ወደቦችን መጠቀም ላይ እየተሰራ መሆኑን መንግስት ሲገልጽ ቆይቷል።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወደቦችን ለአብነትም የበርበራን፣ የሱዳንን፣ የላሙና ሌሎች ወደቦችን እንድትጠቀም ጥረት እያደረገ መሆኑን መንግስት እየገለጸ ነው።
ከሰሞኑም ዘመናዊ ክሬኖች ተገጥመውለታል የተባለው የበርበራ ወደብ አግልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በዚህ ወደብ ላይ 19 በመቶ ድርሻ አላት፤ ጊቤ የተሰኘችው የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ መርከብም ጭነት ይዛ በርበራ ወደብ ደርሰለች።
የምጣኔ ሀብት እና የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት ወደብ ለአንዲት ሀገር ጠንካራ መሆን ትልቅ ሚና አለው።
የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ መምህሩ አቶ እንዳለ ንጉሴ ኢትዮጵያ በርበራን መጠቀም መጀመሯ የኢኮኖሚ ደህንነቷን አስተማማኝ እንደሚያደርው ይገልጻሉ።
አቶ እንዳለ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን መጠቀም መጀመሯ የዕቃዎች ዋጋ እንዲቀንስና አላስፈላጊ ቢሮክራሲዎች እንዳይኖሩ እንዲሁም የንግድ ሁኔታው እንዲቀላጠፍ እንደሚያደርግ አንስተዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች መምህርና የብሉ ናይል ውኃ ምርምር ተቋም ተመራማሪ አቶ አበበ ይርጋ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን መጠቀም መጀመሯ ለወደብ ኪራይ ተብሎ በየዓመቱ ለጅቡቲ የሚከፈለው ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ፤ የምህንድስና እና ሌሎች ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ሳይገቡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አይነት ግድቦች በሁለት አመት ተገንብተው እንዲያልቁ እንደሚያደርግ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ የምትከፍለው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ቢገባ በየዓመቱ ትላልቅ ኢንዲስትሪዎችን መገንባት እንደሚያስችልም አቶ አበበ አንስተዋል።
አቶ እንዳለ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን መጠቀም መጀመሯ በጅቡቲ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረውን የወደብ አገልግት ለማስቀረትም የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የገለጹ ሲሆን ለኢኮኖሚ ውህደትና ትብብርም አይነተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው የተባለው።
አቶ አበበ ይርጋ፤ ኢትዮጵያ የራሷን ወደቦችን እንድታጣ በመደረጓ የገቢና ወጪ ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንዲኖር አድርጎ የነበረ ሲሆን፤ አሁን በርበራን መጠቀም መጀመር ግን ንግዱ እንዲፋጣንና አላስፈላጊ ወጪዎች እንዲቀንሱ እንደሚያደርግ አንስተዋል። ከፖለቲካ አንፃርም ቢሆን ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እንዳይኖራት ተጨማሪ ወደቦችን መጠቀም ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡
አቶ አበበ፤ “ ወደብ ሲኖርህ ኢኮኖሚህ ይሻሻላል፤ ኢኮኖሚህ ፈርጣማ ሲሆን የውስጥ ፖለቲካውም ይረጋጋል፤የውስጥ ፖለቲካና አኢኮኖሚያችን ሲጠነክር ከቀጠናው ላይ ያለን ተሰሚነትና የመወሰን ሃቅምም በዛው ይጨምራል“ ይላሉ።
የወደብ ባለቤት መሆን፤ የጦር መሣሪያን በቀላሉና በጊዜ አስገብቶ ብሔራዊ ደህንነትን ለመከላከል እንደሚያስችል የሚያነሱት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ፤ጊቤ የተሰኘችዋ መርከብ ወደ በርበራ ወደብ መድረሷ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሶሚሊላንድም ኢኮኖሚያዊና ጂዎፓለቲካዊ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሶሚሊላንድና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጂዎስትራቴጂክ አጋር ሆነው እንዲቀጥሉ የበርበራ ወደብ ሁነኛ ሚና ይኖረዋልም ነው የተባለው።