ድጋፉ ለክትባት ዝግጅት እና ምርምር ስራዎች ይውላል ተብሏል
ኢትዮጵያ ለወረርሽ ዝግጁነትና ፈጠራ ጥምረት የገንዘብ ድጋፍ ልታደርግ ነው
ኢትዮጵያ በምርምር ውጤቶች የታገዘና ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚያስችለውን ለወረርሽ ዝግጁነትና ፈጠራ ጥምረት (CEPI) ተቀላቅላለች፡፡ ጥምረቱ ወረርሽኝን በጋራ ለመከላከል ከማስቻልም በላይ ለሚያጋጥሙ አዳዲስ ወረርሽኞች ክትባቶችን የሚያዘጋጅ ነው፡፡
ዛሬ ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ጉዳዩን በማስመልከት በተካሄደ የውይይት መድረክ ኢትዮጵያ ጥረቱን በመደገፍ ረገድ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት የጤና ሚኒስትር ዴዔታዋ ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡፡
ክትባት የጤና ደህንነትን ለመጠበቅ ወሳኝ መሳሪያ ነው ያሉት ዶ/ር ሊያ በህብረተሰቡ ላይ ሊደቀኑ የሚችሉ የወረርሽኝ ስጋቶችን በመቀነስ ረገድ የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ሊያ አዲስ እየተፈጠሩ ላሉ ወረርሽኞች ክትባት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ በመቻላችን ደስተኞች ነን ያሉም ሲሆን አፍሪካ የተፈጠሩ እና ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ወረርሽኞችን መከላከል፣መለየት እና አጥጋቢ ምላሽ መስጠት እንድትችል ለማድረግ በሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ በጋራ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጥምረቱን ጥረት ለመደገፍ እና ለማፋጠን የሚረዳ የ3 መቶ ሺ የአሜሪካ ዶላር (10 ሚሊዬን ብር ገደማ) ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷንም ጥምረቱ አስታውቋል፡፡
ይህ ኢትዮጵያን ለጥምረቱ የገንዘብ ድጋፍን ያደረገች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሃገር ያደርጋታል፡፡
ለዚህም ምስጋናቸውን የቸሩት የጥምረቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሪቻርድ ሃትቼት ኢትዮጵያ ለማህበረሰብ ጤና መጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡ ሊያጋጥሙ ለሚችሉ የወረርሽኝ ስጋቶች ክትባትን ለማቅረብ እና በሃገሪቱ ብሎም በአህጉሪቱ ያለውን የሳይንሳዊ ምርምር ዐቅም ለማጎልበት ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩም ነው ያስታወቁት፡፡
ላጋጠሙና ለሚያጋጥሙ ወረርሽኞች ክትባቶችን ለማዘጋጀት የሚሰራው ጥምረቱ በተለያዩ የመንግስታትና የግል የበጎ አድራጎት ተቋማት ጥምረት እ.ኤ.አ በ2017 በስዊዘርላንድ ዴቮስ የተመሰረተ የምርምር ጥምረት ነው፡፡ ኢቦላን ጨምሮ ወረርሽኝ ሆነው በተከሰቱ የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶችም ላይ ይሰራል፡፡