የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ምሁር ከዶክተሮቹ መካከል ናቸው መባሉን አስተባብለዋል
ባልደራስ “ይቀላቀሉኛል” ያላቸው ዶክተሮች ነገ ይታወቃሉ
ባልደራስ ለእዉነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ”ከአስር በላይ ዶክተሮች በአንድ ጊዜ የአዲስ አበባን ትግል ተቀላቅለዋል“ በሚል በጊዜያዊ ቃል አቀባዩ ስንታየሁ ቸኮል በኩል ከቀናት በፊት አስታውቆ ነበር፡፡
የተጠቀሱት ዶክተሮች ’የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እንደሚሆኑ ታውቋል‘ የሚል ጽሁፍንም ነበር አቶ ስንታየሁ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ያስታወቁት፡፡
አል ዐይን አማርኛም ባልደራስን “ይቀላቀላሉ” የተባሉት ዶክተሮች እነማን ናቸው በሚል ቃል አቀባዩን ጠይቋል፡፡
የተባሉትን ሰዎች ’ማንነት ማስታወቁ አስፈላጊም አይደለም‘ ያሉት ቃል አቀባዩ ’መስራች የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት ይፋ ማድረጉ አግባብ አይደለም‘ ስለመባሉም ነው የገለጹት፡፡
የፓርቲው መስራችጠቅላላ ጉባዔ ነገ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጠዋት ጀምሮ አዲስ አበባ ቸርችል ሆቴል አካባቢ በሚገኘው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጽህፈት ቤት ቅጥረ ግቢ ውስጥ ይካሄዳል፡፡
ባልደራስን ይቀላቀላሉ የተባለላቸው እነዚህ ዶክተሮችም በዚሁ ጉባዔ ተጠቁመው በእጩነት ከቀረቡ በኋላ ለውክልና ተወዳድረው የሚመረጡ እንደሆነም ነው አቶ ስንታየሁ የገለጹልን፡፡
ባልደራስን እንደሚቀላቀሉ ከተነገረላቸው ዶክተሮች መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር የሆኑት ዶክተር ደረጄ ዘለቀ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ሊሆኑ እንደሚችሉ በተለያዩ ማህበረሰባዊ የትስስር ገጾች የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ዶ/ር ደረጄ የመንግስትን ህግና ስርዓት ያለማስከበር ክፍተቶች በመተቸት ይታወቃሉ፡፡
ምክንያታዊ ናቸው በሚባሉ ምሁራዊ ትችቶቻቸውም ብዙዎች ያውቋቸዋል፡፡
የመረጃዎቹን እውነታነት ለማረጋገጥም አል ዐይን አማርኛ ዶክተር ደረጄን በስልክ ጠይቋል፡፡
የሚባለው ነገር ’ዝም ብሎ‘ እንደሆነና ጠንከር ያሉ አስተያየቶችን ሲሰጡ የሚያውቋቸው ሰዎች እንደዛ ቢሉ እንደማይገርማቸው የገለጹት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ታዲያ ‘እንደ አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪነቴ መብቴን የሚያስጠብቅልኝን ፓርቲ እንደግፋለሁ፤ ሙሉ ድጋፍ አደርጋለሁ፤ በዚህ ደግሞ ከባልደራስ የተሻለ የለም’ ብለዋል፡፡
ሆኖም ፓርቲ የመቀላቀል ፍላጎት እንደሌላቸው ነው የተናገሩት፡፡
በነገው የባልደራስ መስራች ጉባዔ ይሳተፉ እንደሆነ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ግን ‘አዎ!‘ የሚል ምላሽን ሰጥተውናል፡፡