ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ አብራርተዋል
የተርባይኖች ቁጥር ቢቀንስም ግድቡ ተመሳሳይ የሀይል መጠንን ያመነጫል-ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ
የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ፣የድርድር ሂደት እና ጠቀሜታ እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ተቋም ባዘጋጀው ወርሃዊ ዐውደ ጥናት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የግድቡ የተርባይኖች ቁጥር ወደ 13 እንዲቀንስ መደረጉን ተከትሎ ግድቡ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ያሉት ሚኒስትሩ፥ እስከ 210 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመቆጠብ የሚያስችል መሆኑን ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ እንዳቀረቡት ማብራሪያ ከሆነ የተርነባይኖቹ ቁጥር ከ16 ወደ 13 ቢቀንስም የማመንጨት ዐቅማቸውን በማሳደግና የስራ ሰዓታቸውን ከፍ በማድረግ ቀደም ሲል ታስቦ የነበረውን በሰዓት 15 ሺ 692 ጊጋ ዋት ሀይል ማመንጨት ይቻላል፡፡ የተርባይን ቁጥሩ ሲቀነስና ሳይቀነስ ሊመነጭ የሚችለውን የኢነርጂ መጠንም በንጻሬ አስቀምጠዋል፡፡
የተርባይኖቹ ቁጥር ሳይቀንስ
ግድቡ ቀደም ሲል ተደረገለት በተባለው የዲዛይን ማሻሻያ 6 ሺ 350 ሜጋ ዋት ኃይልን እንደሚያመነጭ ታስቦ ነበር፡፡ ይህ ኃይል የሚመነጨውም በወቅቱ ይተከላሉ በተባሉ አስራ ስድስት ተርባይኖች በኩል ነው፡፡ ከአስራ ስድስቱ ተርባይኖች መካከል አስራ አራቱ እያንዳንዳቸው 4 መቶ ሜጋ ዋት ሁለቱ ደግሞ እያንዳንዳቸው 3 መቶ 75 ሜጋ ዋት አመንጭተው ነው በድምሩ 6 ሺ 350 ሜጋ ዋት ኃይልን የሚያስገኙት፡፡ ተርባይኖቹ በሰዓት 15 ሺ 692 ጊጋ ዋት ኃይልንም ያመነጫሉ፡፡
ሆኖም ይህን ሀይል ለማግኘት ተርባይኖቹ ከዓመቱ ቀናት ውስጥ 28 ነጥብ 2 በመቶ ያህሉን ወይም በዓመት ውስጥ 2 ሺ 471 ሰዓታትን አለበለዚያም በዓመት ውስጥ 103 ቀናትን መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የተርባይኖቹ ቁጥር ሲቀንስ
የተርባይኖቹ ቁጥር ወደ 13 ዝቅ ሲል ግድቡ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ይላሉ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፡፡ ይህን ለማግኘትም 11ዱ ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 4 መቶ ሜጋ ዋት ቀሪዎቹ ሁለት ተርባይኖች ደግሞ እያንዳንዳቸው 3 መቶ 75 ሜጋ ዋት ኃይልን ማመንጨት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚመነጨው የኃይል መጠን ግን ቀደም ሲል ታቅዶ ከነበረው (6 ሺ 350) በ1ሺ 2 መቶ ሜጋ ዋት ያነሰ ነው፡፡ይህ የተርባይኖቹ የማመንጨት ዐቅም እና የስራ ሰዓት ባለበት ሆኖ ነው፡፡
ሆኖም የተርባይኖቹን የስራ ሰዓት ከዓመቱ ቀናት ውስጥ 34 ነጥብ 8 በመቶ ወይም በዓመት ውስጥ 3 ሺ 66 ሰዓት አለበለዚያም በዓመት ውስጥ 128 ቀናት በማድረግ ተርባይኖቹ በሰዓት እንዲያመነጩ ታስቦ የነበረውን 15 ሺ 692 ጊጋ ዋት ኢነርጂን ማግኘት እንደሚቻል ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ጠቁመዋል፡፡
የግንባታ እና የድርድር ሂደት
ከግንባታ መዘግየት ጋር በተያያዘ የሀገር ውስጥ አቅምን ለመገንባት በሚል የአሌክትሮ መካኒካል ስራው ለሜቴክ መሰጠቱ ሀገሪቱን ዋጋ እንዳስከፈለ ያነሱት ሚኒስትሩ የምህንድስና ሳይንስ እና መልካም ፍላጎት ይለያያሉ ብለዋል።
ሜቴክ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ስራዎችን አለማከናወኑ፥ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ውጭ በመላክ ልታገኝ የምትችለውን እስከ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንድታጣ፣ የግንባታ ተቋራጩ ተጨማሪ ክፍያ እንዲጠይቅ፣ የተዘረጋው የሀይል ማስተላለፊያ መስመር ስራ እንዲፈታ እና ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ወደ ተወሳሰበ ድርድር እንድትገባ አስገድዷታልም ነው ያሉት።
ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር እየተደረገ ስላለው ድርድር ያነሱት ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድብ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስምምነት ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ነው የገለፁት።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከሀይል ማመንጨት በተጨማሪ ለአሳ ሃብት ልማት እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
እንደ ኤፍ.ቢ.ሲ ዘገባ ከሆነ በመድረኩ ላይ የተካፈሉ የፖሊሲ አውጭዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና አጥኚዎች በአጠቃላይ የግድቡ ሁኔታ እና በግድቡ ዙሪያ ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር እየተደረገ ባለው ድርድር ላይ ጥያቄዎችን ሰንዝረው እና አስተያየቶችን ሰጥተው ውይይት ተደርጓል።
ከኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎች ቡድን ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው፣ አቶ ተፈራ በየነ እንዲሁም የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡት ወቅት ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡