የህዳሴ ግድብ የመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍቻ መሆን የለበትም!
አብሮነት የህዳሴው ግድብ ድርድር እንዲራዘም ጠየቀ
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በመካሄድ ላይ ያለው ድርድር እንዲራዘም ጠየቀ፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ በመካሄድ ላይ ያለው ድርድር በቶሎ እንዲጠናቀቅ በከፍተኛ ፍጥነት እየተካሄደ ነው ያለው ጥምረቱ ግድቡ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ፋይዳ ያለውና በዋጋ ሊተመን የማይችል የህዝብ ፕሮጀክት በመሆኑ ድርድሩ የወደፊቱን ትውልድ እንዲሁም ሌሎቹንም የተፋሰሱን ሃገራት እንደሚመለከት አስታውቋል፡፡
አሸማጋይ ሃገራቱ እና የፋይናንስ ተቋማቱ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለግብጽ የቀረበ ወዳጅነት ያላቸውና ድርድሩን ለመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍቻነት ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ናቸው ያለም ሲሆን ቀድሞውኑ ኢትዮጵያ ጥያቄውን መቀበል አልነበረባትም ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ሊያስጠብቅ የሚችል ውጤት የማይገኝበትንና በሩቅ እና ገለልተኛ ባልሆኑ ኃይሎች እንዲካሄድ የተፈለገውን ድርድር ቀድሞውኑ መቀበል አልነበረባትም፤ስምምነት ላይ መደረሱም ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው ብሎ እንደሚያምንም ነው ያስታወቀው፡፡
በመሆኑም ከአገር ብሔራዊ ደህንነት ጋር የተያያዘ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ በጥድፊያ እና ግልፅነት በጎደለው ሁኔታ መወሰን እንደሌለበት በመግለጽ
1. የድርድሩን ሰነድ በስምምነት ለመቋጨት የተያዘው ግዜ ላልተወሰነ ግዜ እንዲራዘም፤በዚህ በሚራዘመው ግዜም በቂ መድረክ ተፈጥሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ከህዝብ እና ከአፍሪካ ወዳጅ አገሮች ጋር ጭምር ግልፅ ውይይትና ምክክር እንዲካሄድ፤
2. የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን ጉዳይ በትኩረት እንዲከታተልና ይህ ስምምነት ከእሱ ዕውቅና ውጭ በጥድፊያ እንዳይፈረም በመንግስት ላይ የራሱን ተፅዕኖ እንዲፈጥር ጠይቋል፡፡
አብሮነት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) እና ኅብር ኢትዮጵያ ‹‹የኢትዮጵያ ኮንፌዴራሊስት ኃይሎች በሀገሪቱ ኅልውና ላይ ሊፈጥሩት የሚችሉትን አደጋ ለመቋቋም አልመናል›› በሚል የመሰረቱት ጥምረት መሆኑ ይታወቃል፡፡