ብልጽግና በአንዱ የአዲስ አበባ ወረዳ ካሸነፈ ከአመራርነት ለመልቀቅ ቃል ገብተናል
መሪው ፓርቲ እንዲሸነፍ እንሰራለን-ባልደራስ
”መሪው ፓርቲ እንዲሸነፍ“ ለማድረግ እንደሚሰራ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) አስታውቋል፡፡ ምሁራንን ማሰባሰብን ጨምሮ ለዚህ የሚሆን ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን ያስታወቀው ፓርቲው የመጀመሪያ መስራች ጉባዔውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡
ጉባዔው በስኬት መካሄዱን በስፍራው ተገኝተው ለነበሩት ብዙሃን መገናኛዎች በሰጠው መግለጫ የገለጸው የፓርቲው ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ (የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሆኖ ተመርጧል) በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ መጽደቁን አስታውቋል፡፡
የተጨበጠ እጅ የፓርቲው መለያ አርማ (ሎጎ)እንዲሆንም ተወስኗል፡፡
የፓርቲውን የብሄራዊ ምክር ቤት እና ኦዲትና ኢንስፔክሽን ቁጥጥር አባላትን ለማስመረጥ የሚችል ኮሚቴ ተመርጦ ድምጽ መሰጠቱንም ነው ያስታወቀው፡፡
በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ያሉ ምሁራን በእጩነት ቀርበዋለ፡፡ ከቀረቡት መካከል 12ቱ የ3ኛ ዲግሪ (ዶክትሬት)፣12ቱ 2ኛ ዲግሪ (ማስትሬት) ያላቸው እና ቀሪዎቹ አስሮች የህግ ምሁራን 6 የሚሆኑት ደግሞ መሃንዲሶች ናቸው ተብሏል፡፡ የምሁራኑን ዝርዝር ግን ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል፡፡ከጉባዔው መጠናቀቅ በኋላ አሳውቃለሁም ነው ያለው፡፡
ምሁራኑ አዲስ አበባን ብቻም ሳይሆን ሃገር ለመረከብ ጭምር ባላቸው ብቃት የተመረጡ ናቸው ያለው እስክንድር በዚህ ረገድ ብልጽግናን ጨምሮ ይሄን ያህል ያሰባሰበ ፓርቲ እንደሌለ ነው የተናገረው፡፡
ባልደራስ ምሁራንን በአመራርነት ማሰባሰቡ መልካም ቢሆንም ምሁር መሆን ብቻውን ውጤታማ ሊያደርግ እንደማይችል እና ህዝብ የሚፈልገውን ለመስጠት ዋስትና እንደማይሆን በመጠቆም ለቀረበለት ጥያቄም ምሁር መሆን ብቻውን ውጤታማ ባያደርግም ለጊዜው የህዝብን ጥያቄ ይመልሳል፤ ውጤታማነቱ በሂደት እንዲለይ ለማድረግም እንሰራለን ብሏል፡፡
ባልደራስ ክልላዊ ፓርቲ ሆኖ ነው በቅርቡ የተመሰረተው፡፡ ሆኖም ይህ በጊዜ ማጠር ምክንያት መሆኑን አስታውቋል፡፡በአዲስ አበባ ቢመሰረትም ተሳትፎውን ሃገራዊ ለማድረግ በሌሎች ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ ብልጽግና/ኢህአዴግ/ን ለማሸነፍ ይሰራልም ነው ያለው፡፡
ከየትኞቹ ድርጅቶች ጋር ሊቀናጅ እንደሚችል ለቀረበለት ጥያቄ ግን ድርጅቶቹን የመለየትና የመወያት ስራ እንደሚሰራ ከማስታወቅ ውጭ ያለው ነገር የለም፡፡
በምርጫው ማግስት ሃገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ ለመንቀሳቀስ እና ከከተማ አቀፍ ወደ ሃገር አቀፍ ፓርቲነት እንሰራለን ያለው እስክንድር ብልጽግና/ኢህአዴግ/ እንዲሸነፍ በአንዱም የአዲስ አበባ ወረዳዎች እንዳያሸንፍ ለማድረግ እንሰራለን ብሏል ካሸነፈ አመራሩ ለመልቀቅ ቃል መግባቱን በመጠቆም፡፡
ህገመንግስት አንጥስም በሚል ሃገራዊ ምርጫው በክረምት ይካሄድ መባሉንም ነቅፏል፡፡
ገዢው ፓርቲ ህገመንግስቱን መቼ አከብሮት ያውቃል ያለም ሲሆን ባልደራስ ስብሰባ እንኳን እንዳያደርግ የተከለከለባቸውን ጊዜያት በማሳያነት አንስቷል፡፡
በመስራች ጉባዔው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካይ በታዛቢነት መገኘቱን አስታውቋል፡፡