“ያልተሳካለት በሁለት ሳምንት የአባቶቼን ርስት እወርሳለሁ ያለው ሃይል ነው” -ጠ/ሚ አብይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ከታጠቁ ሃይሎች ጋር የሚደረገው ንግግር ይቀጥላል ብለዋል
ኢሰመኮ በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች በአማራ ክልል የጅምላ እስር እና የንጹሃን ግድያ መቀጠሉን መግለጹ ይታወሳል
በአማራ ክልል ከአንድ አመት በላይ የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም አሁንም መንግስት ለሰላማዊ አማራጮች ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ መንግስታቸው ከታጠቁ ሃይሎች ጋር ንግግር ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
“ማንም እንደማያሸንፈን እናውቃለን፤ የሚሻለን ግን ሰላም ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሃይሎች ጋር ንግግሮች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ህብረት እና በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በኩል ሙከራዎች መደረጋቸውን በማውሳትም ይሄው ጥረት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የሰላም ንግግሮችን የሚያደናቅፉ ያሏቸው ሃይሎች “የሀገር ሽማግሌዎችን በእንብርክክ” መመለሳቸውን ነው ያነሱት።
አብንን የወከሉት የምክርቤት አባል በአማራ ክልል የጅምላ እስርና የንጹሃን ግድያ ቀጥሏል፤ መንግስት በሁለት ወር ውስጥ ክልሉን እንቆጣጠራለን ቢልም ጦርነቱ ከአንድ አመት በላይ ሆኖታል የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሰጡት ምላሽ አማራ ክልል ፓርቲያቸው ብልጽግና ያሸነፈበት መሆኑን በመጥቀስ ከማን አስለቅቆ ሊቆጣጠር ይችላል በሚል ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል።
“በሁለት ሳምንት ውስጥ የአባቶቼን ርስት እወርሳለሁ ያለው ሀይል ነው ያልተሳካለት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግስት የአማራ ክልልን የኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ ላይ ማተኮሩን አብራርተዋል።
“መንግስት በወታደሮች ታጅቦ ማዳበሪያ እያደረሰ ነው፤ ይሁን እንጂ ልማት እንዳይሰራ የሚያደናቅፉት ሃይሎች አሉ” በሚልም የታጠቁ ሃይሎችን ወቅሰዋል።
አማራ በኢትዮጵያ ምስረታና ታሪክ ያለውን ድርሻ አቅልለን አንመለከትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ በክልሉ የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን በሚያደናቅፉ ሃይሎች ላይ እርምጃው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክርቤት አባሉ ከጅምላ እስር ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ “በጅምላ የምናስር ቢሆን እርሶም ይታሰሩ ነበር፤ በግብር ነው የምናስረው፤ መኖሪያ ቤቶችን እንደምንገነባው ሁሉ ማረሚያ ቤቶችንም እንገነባለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና በድሮኖች በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ንጹሃን እየተገደሉ ነው ለሚለው ጥያቄ ግን በቀጥታ ምላሽ አልሰጡም።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች በክልሉ እየተካሄደ ባለው ጦርነት በርካታ ንጹሃን መገደላቸውንና የጅምላ እስሩ መቀጠሉን መግለጹ ይታወሳል።
በክልሉ የመንግስት ተቋማት አመራሮች እና ነጋዴዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ከታሰሩም አንድ ወር እንዳለፋቸው አል አይን አማርኛ ያነጋገራቸው የክልሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን ዳግም አደራጃለሁ በሚል ውሳኔ ካሳለፈበት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች አማካኝነት ጦርነት መቀስቀሱ ይታወሳል።