ኢትዮጵያ አበዳሪ ተቋማት ቃላቸውን እንዲያከብሩ ጠየቀች
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፓሪስ እየተካሄደ ባለው የአለማቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባኤ እየተሳተፉ ነው
በጉባኤው የአለም ባንክን ጨምሮ አለማቀፍ አበዳሪ ተቋማትና ከ40 በላይ የሀገራት መሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው
ኢትዮጵያ አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የተደረሱ ስምምነቶች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ጠይቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው “አዲስ የአለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባኤ” ላይ ሲሳተፉ ነው ስምምነቶቹ እንዲተገበሩ የጠየቁት።
ኢትዮጵያ በ2019 ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የመጀመሪያ ምዕራፍ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የ3 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ አይኤምኤፍም ሆነ የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚያደርጉት የፋይናንስ ድጋፍ በተለይ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ተቋርጧል።
ሀገሪቱ ከውጭ ድጋፍ ለማግኘት ካቀደችው ውስጥ ያገኘችው 22 ከመቶውን ብቻ መሆኑንም በቅርቡ አሳውቃለች።
ይህም ከፍተኛ የበጀት ጉድለት መፍጠሩ የተነገረ ሲሆን፥ መንግስት ከአለማቀፍ ተቋማት ድጋፍ ለማግኘት የሚያደርገው ድርድር መቀጠሉ ተገልጿል።
በፓሪስ እየተካሄደ ባለው አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጉባኤም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አበዳሪ ተቋማት የተፈራረሙትን ስምምነት ገቢራዊ እንዲያደርጉት መጠየቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአነስተኛ ወለድ የሚቀርብ የኮንሴሽናል ብድር አቅርቦት እንዲያድግ መጠየቃቸውም ነው የተነሳው።
ለአረንጓዴ ልማት የሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍ ሊያድግ ይገባልም ብለዋል።
በፓሪሱ ጉባኤ የኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ ሀገራት (በተለይም የአፍሪካ ሀገራት ) መሪዎች እየተሳተፉ ሲሆን፥ የአለም ባንክ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሀገራት ይፋ የሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ ይጠበቃል።
አዲሱ የባንኩ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ የእዳ መመለሻ ጊዜ ማራዘሚያን የተመለከቱና ሀገራት ድንገተኛ አደጋ ሲገጥማቸው ሊደረግላቸው ስለሚችለው ድጋፍ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሏል።
የአለም ባንክ በፓሪሱ ጉባኤ ይፋ የሚያደርጋቸው ማሻሻያዎች ለታዳጊ ሀገራት መጠነኛ እፎይታ ይሰጡ ይሆናል እንጂ ከገቡበት የፋይናንስ ቀውስ የሚታደግ እንደማይሆን ግን ሬውተርስ ዘግቧል።
የአለማችን ቀዳሚዋ አበዳሪ ሀገር ቻይና የምታነሳውን አለማቀፍ አበዳሪዎች “የታዳጊ ሀገራቱን እዳ ይቀንሱ፤ ኪሳራቸውን ይጋሩ” ሃሳብንም አሜሪካና ዋነኞቹ አበዳሪዎች አይቀበሉትም ብሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም የአለማቀፉ የፋይናንስ ስርአት ወቅቱን የማይመጥን እና ኢፍትሃዊ መሆኑን ነው በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት ያነሱት።
“የአለም የፋይናንስ ስርአት ተልዕኮውን ማሳካት አልቻለም፤ ለታዳጊ ሀገራት የሴፍቲኔት ፕሮግራሞችም ድጋፍ ማድረግ ተስኖታል” ሲሉም ተደምጠዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው፥ አበዳሪ ተቋማት ለድሃ ሀገራት እዳ እንዲሰርዙ ጠይቀዋል።
በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋን ለመቋቋም ለሀገራቱ የሚደረገው ድጋፍ ሊያድግ እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት።
ዛሬ በፓሪስ የተጀመረው “አዲስ የአለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ስምምነት ጉባኤ” በነገው እለት የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚውል የ100 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ቃል ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
በፈረንጆቹ 2009 እና በ2015ቱ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለታዳጊ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ ቃል መገባቱን የሚያወሳው የመንግስታቱ ድርጅት፥ እስካሁን ግን ተፈጻሚ ሲሆን አልታየም ብሏል።