ውይይቱ በአበዳሪ ሀገራት ኮሚቴ የሚደረግ ነው
የአበዳሪ ሀገራት ኮሚቴ ኢትዮጵያ ባቀረበችው የብድር ሽግሽግ ጥያቄ ላይ ሊወያይ ነው ተባለ፡፡
ኮሚቴው በመጪው ሰኞ በኢትዮጵያ ጥያቄዎች ላይ እንደሚመክር ሮይተርስ የመረጃ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
ኮሚቴው ከአሁን ቀደም ለሶስት ያህል ጊዜያት በኢትዮጵያ ጥያቄዎች ላይ መክረዋል፡፡
በቅርቡ ከገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ጋር ተገናኝተው የመከሩት የፓሪስ የአበዳሪዎች ክለብ ተባባሪ ሊቀመንበር ሚስተር ዊሊያም ሮስ እስካሁን ሶስት ጊዜ ተገናኝቶ እንደመከረ አስታውሰው አራተኛ ስብሰባውን በቅርቡ እንደሚያደርግና ከዚህ በፊት በተደረጉት ውይይቶች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መታየቱን ተናግረው እንደነበር ሚኒስቴሩ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ምክክሩ በኮሮና ወረርሽኝ እና በጦርነት እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ምጣኔ ሃብታዊ ጫናዎች የበዙባት ኢትዮጵያ የዕዳ ተጋላጭነት ሳይኖራት ግዴታዎቿን ልትወጣና ብድሯን ልትመልስ በምትችልባቸው መንገዶች ዙሪያ የሚደረግ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ፈረንሳይና ቻይና የሚመሩት የአበዳሪዎች ኮሚቴ በቡድን 20 አባል ሃገራት የብድር ማዕቀፍ መንገድ ያለባትን የብድር እዳ እንዲያሸጋሽግላት መጠየቋ የሚታወስ ነው፡፡
ኮሚቴውም ጥያቄውን በመያዝ ባሳለፍነው መስከረም ወር የመጀመሪያ ስብሰባውን አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ጦርነቱን ተከትሎ ያን ያህል የኢትዮጵያን የእዳ ጫናዎች ሊቀሉ የሚችሉ ተጫበጭ እርምጃዎችን ሳይወስድ ቀርቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ)ን እና ዓለም ባንክን ጨምሮ ሌሎች የገንዘብ ተቋማት ኮሚቴው በኢትዮጵያ፣ ቻድ እና ዛምቢያ ለቀረቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽን እንዲሰጥ ግፊት ሳያደርጉ ቆይተዋል፡፡
የአይ.ኤም.ኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫን ጨምሮ የአሜሪካ ግምጃ ቤት (ትሬዥሪ ዲፓርትመንት) ዋና ጸሃፊ ጃኔት የለን ሁሉ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ጭምር ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን በማስታወስ ግፊት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም ነው ኮሚቴው በመጪው ሰኞ ለ4ኛ ጊዜ እሰበሰባለሁ ያለው፡፡
ጉዳዩ በዚህ ሳምንት በኢንዶኔዥያ ባሊ እንደሚሰባሰቡ የሚጠበቁት የቡድን 20 አባል ሃገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ቀዳሚ የውይይት አጀንዳ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡