መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ የጀመረውን ሂደት አራዘመ
የገንዘብ ሚኒስቴር፤ ተቋማትን ወደ ግል ለማዞር የተጀመረውን ሂደት ለማጠናቀቅ “ዝግጁ ነኝ” ብሏል
አሁን ባለው ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ምክንያት ሂደቱ ቆሟል ተብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለግል ባለሀብቶች ለመሸጥ የጀመረውን ሂደት ለሌላ ጊዜ ማራዘሙን አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የቴሌኮም ዘርፍን ለግል ባለሀብቶች ለመሸጥ የተጀመረው ሂደት እንዲራዘም መወሰኑን ገልጿል።
መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ወደ ግል ለማዘዋወር የተጀመረውን ሂደት ለማራዘም የወሰነው በሀገር ቤት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ለውጦች ምክንያት መሆኑንም አስታውቋል።
መንግስት በ “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር” ውስጥ ካካተታቸው ጉዳዮች አንዱ የቴሌኮም ዘርፍን ወደ ግል የማዞሩ ስራ አንዱ ነው። ይሁንና ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ “ታይተዋል” ባላቸው ለውጦች ምክንያት ለጊዜው እንዲቆምና ለሌላ ጊዜ እንዲዛወር ወስኗል።
አንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ዕድሜ ያለው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን 40 በመቶ ድርሻው እንዲሸጥ ሲወሰን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥ አደረገች በሚል ሲወራ ነበር።
በአፍሪካ በተለያዩ ሀገራት በቴሌኮም ዘርፍ የተሰማራው ሳፋሪኮም የተባለ ኩባንያ በኢትዮጵያ ለመስራት ተመዝግቦ ራሱን እያስተዋወቀ ነው። ከአንድ ወር በኋላ ሳፋሪኮም በአዲስ አበባ እና በተመረጡ ከተሞች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቴሌኮም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዘርፎችም ክፍት ሊደረጉ ስለሚችሉ የኢትዮጵያ ተቋማት ከወዲሁ ዝግጁ እንዲሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንጻን ሲመርቁ የፋይናንስ ዘርፎች ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ሊደረጉ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጡ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ኩባንያዎች ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባቸው ገልጸው ነበር።
መንግስት ተቋማትን ወደ ግል የማዞሩን ስራ ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።