ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪኳ ከፍተኛ ውጤት ማስመዘገቧ ተገለፀ
ኢትዮጵያ በኦሬገን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዓለም 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀች
በኦሬጎን አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 4 ወርቅ፣ 4 ብርና 2 ነሃስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን አሸንፋለች
በአሜሪካ አስተናጋጅነት በኦሬጎን ሲካሄድ የቆየው 18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሌሊት ላይ በተካሄዱ ውድድሮች ፍጻሜውን አግኝቷል።
ላለፉት 10 ቀናት በአሜሪካ ኦሪገን ሲካሄድ በነበረው 18ኛውን የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በታሪኳ ከፍተኛውን ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች።
በውድድሩ ኢትዮጵያ 4 የወርቅ፣ 4 የብር እና 2 የነሃስ በድምሩ በ10 ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ ከአዘጋጇ አሜሪካ በመቀጠል ከዓለም 2ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በወንዶች ማራቶን በአትሌት ታምራት ቶለ፣ በሴቶች ማራቶን በአትሌት ጎትይቶም ገ/ስላሴ እንዲሁም በሴቶች 1000 ሜትር በአትሌት ለተሰንበት ግደይ እና በ5 ሺ ሜትር ሴቶች በአትሌት ጉዳፍ ፀጋይ አግኝታለች።
በ3ሺ ሜትር መሰናክል በሴት እና ወንድ እንዲሁም በወንዶች ማራቶን እና በ1500 ሜትር ሴቶች የብር ሜዳሊያ የተገኘ ሲሆን፤ ሁለቱ የነሐስ ሜዳያ የመጣው ደግሞ በሴቶች 3ሺ መሰናክል እና በ5ሺ ሜትር ነው የተገኙት።
የሻምፒዮናው አስተናጋጅ አሜሪካ በ13 ወርቅ፣ በ9 የብር እና 11 የነሃስ ሜዳሊያዎች በድምሩ በ33 ሜዳሊያ አንደኛ ደረጃን በማያዝ ማጠናቀቅ ችላለች።
ኬንያ ደግሞ በ2 ወርቅ ፣5 የብር እና 3 የነሀስ በድምሩ 10 ሜዳሊያ በማግኘት ከዓለም 4ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ድሉን በማስመልከት ትናንተ በሰጠቸው አስተያየት፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብላለች።
በኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክ ሻምፒዮና ታሪክ ያገኘችው ከፍተኛ ውጤት መሆኑን እና ይህም የሁሉም አትሌቶች፣ የልኡካን ቡድኑ አባላት እና የአትሌቶች ቤተሰቦቸ ውጤት ነው ብላለች።
2015 አዲስ ዓመት ለመግባት አንድ ወር መቅረቱን በመንሳትም በሻምፒዮናው የተገኘው ውጤት ለመላው ኢትዮጵያውን ለአዲስ ዓመት ያበረከትነው ስጦታ ነው ስትልም ተናግራለች።