አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ኦሎምፒክን ጨምሮ 10 ዓለም አቀፍ ውድድሮችን አሸንፏል
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ዛሬ በኒዮርክ ማራቶን ለአሸናፊነት ይጠበቃል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አምና ሳይካሄድ የቀረው 50ኛው የኒዮርክ ማራቶን ዛሬ እንደሚካሄድ የውድድሩ አዘጋጆች መርሃግብር ያስረዳል።
በዚህ ውድድር ላይ አትሌት ቀነኒሳን ጨምሮ ለኔዘርላንድ የሚሮጠው ትውልደ ሶማሊያዊው አብዲ ናጊየ ለአሸናፊነት ይጠበቃሉ።
ቀነኒሳ ለዚህ ውድድር አስቀድሞ ወደ ኒዮርክ ያቀና ሲሆን፤ ከውድድሩ በፊት በሰጠው አስተያየት “በእስካሁኑ የአትሌትነት ህይወቴ ባስመዘገብኩት ድል ደስተኛ ነኝ ነገር ግን በኒዮረክ ማራቶን ከዚህ በፊት ተሳትፌ አላውቅም “ ብሏል።
ከአንድ ወር በጀርመን በተካሄደው የበርሊን ማራቶን ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አትሌት ቀነኒሳ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በሚፈልገው ልክ ልምምድ አለመስራቱ አሸናፊ እንዳይሆን እንዳደረገው ተናግሮ ነበር።
ለኒዮርክ ማራቶን በቂ ዝግጅት ማድረጉን የተናገረው አትሌት ቀነኒሳ ውድድሩን ለማሸነፍ እንደሚሮጥም አክሏል።
የ39 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በማራቶን ውድድር ታሪክ ሁለተኛው ፈጣን ሯጭ ሲሆን ሁለት የማራቶን ውድድሮችን፣ሶስት የኦሎምፒክ ውድድሮች፣ እና አምስት የአገር አቀፍ አቋራጭ ውድድሮችን ማሸነፉ የታወሳል።