የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል አምቡላንሶቹ ከጥቃት እንዲጠበቁለት ጠየቀ
ማህበሩ ደም ልገሳን ጨምሮ ሌሎች ድጋፍ እንዲደረግለት በጎ ፈቃደኞችን ጠይቋል
በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ማሻቀቡን ማህበሩ አስታውቋል
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል አምቡላንሶቹ ከጥቃት እንዲጠበቁለት ጠየቀ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል በተከሰተው ጦርነት እና ድጋፍ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
የማህበሩ ዋና ጸሀፊ አቶ ጌታቸው ተአ እንዳሉት በአማራ ክልል በተከሰተው ጦርነት የቆሰሉ ሰዎች፣ የተጠፋፉ እና ሌሎች ጉዳቶች የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል ።
በዚህም መሰረት የህክምና እና ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመርዳት ቀይ መስቀል ማህበር ተሽከርካሪዎቹን በማንቀሳቀስ ላይ በመሆኑ ተፋላሚ ወገኖች ከጥቃት እንዲጠብቁት ማህበሩ ጥሪ አቅርቧል።
ባለፉት ቁናት በአማራ ክልል በነበረው ጦርነት ምን ያህል ሰው ህይወቱ አለፈ? የቆሰሉም ምን ያህል ናቸው? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ " በክልሉ ካሉን የቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ጋር ያለን ግንኙነት የተቆራረጠ ነው የተሟላ መረጃ የለንም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በቀይ መስቀል ተሽከርካሪዎች የጦር መሳሪያ፣ ወታደሮችን እና ታጣቂዎችን ማጓጓዝ ክልክል መሆኑን የገለጸው ማህበሩ ዓላማችን ተጎጂዎችን መርዳት በመሆኑ ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጥሪ አቅርቧል።
አሁን ላይ የቆሰሉ ሰዎችን ለመርዳት በክልሉ የደም እጥረት እና የህክምና ቁሳቁስ እጥረት በማጋጠሙ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ በጎ ፈቃደኞች የደም ልገሳ እና ምግብ ነክ ድጋፎች እንዲያደረጉለትም ቀይ መስቀል አሳስቧል።
በጦርነት ቀጠና ውስጥ ያሉ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ለመርዳት መንገዶችን ከመክፈት ጀምሮ ተፋላሚ ወገኖች የህክምና ተቋማት ከየትኛውም አደጋ መጠበቅ አለባቸው ሲሉም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
የሚንስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታዉሳል።
ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያወጀው የክልሉን ደህንነት ሁኔታ በመደበኛ የጸጥታ መዋቅር ማስከበር እንደማይቻል መገለጹን ተከትሎ ነው።