ከትግራዩ ጦርነት ጀምሮ 15 ሰራተኞቹ እንደተገደሉበት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ገለጸ
ማህበሩ የተለያዩ አካላት ባደረሱት ጥቃት ግጭት ባለባቸው ከልሎች ከ100 በላይ አምቡላንሶች ወድመውብኛል ብሏል
ማሕበሩ በሰራተኞቹ ላይ የሚደርሰው ግድያ እና እገታ መባባስ መሰረታዊ ድጋፎችን ለማሰራጨት ፈተና እንደሆነበት ገልጿል
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ግጭት ባለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የህይወት አድን ስራዎችን ለመሰራት በከፍተኛ ሁኔታ እየተቸገረ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ማህበሩ ባለፉት 4 እና 5 አመታት በትግራይ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች መድሀኒቶችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በታጠቁ አካላት በተደጋጋሚ የጥቃት ኢላማ ተደርጊያለሁ ብሏል፡፡
በትግራዩ ጦርነት ጊዜ ከ100 በላይ አምቡላንሶች መውደማቸውን ወይም መቃጠላቸውን እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ የማህበሩ ጽህፈት ቤቶች ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን እና የመድሀኒት መደብሮች ላይ ዝርፊያ ማጋጠሙን የማህበሩ የሰብዓዊ ዲፕሎማሲና የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ መስፍን ደረጄ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
በሾፌሮች፣ በማሕበሩ ሠራተኞችና በጎ ፈቃደኞች ላይ ከሚደርሰው ጥቃት ባለፈ የማሕበሩ አምቡላንሶች በታጣቂዎች መወሰዳቸውን፣ በጥይት መመታታቸውንና መቃጠላቸውን ነው ኃላፊው የሚያነሱት፡፡
በዚህ አመት በአማራ ክልል እየተካሄደ በሚገኘው ግጭት እስካሁን ከአራት በላይ አምቡላንሶች ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ኃላፊው ብዙ ጊዜ አለምቀፋዊ ምልክታችንን በመመልከት ገለልተኛ መሆናችንን የተረዱ አካላት ይተባበሩናል፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ዝርፊያ እገታ እና ግድያን እያስተናገድን እንገኛለን፤ ይህ ለስራችን በከፍተኛ ሁኔታ ተግዳሮት ሆኗል ብለዋል፡፡
በትግራይ የነበረው ጦርነት የፌደራል መንግስትና ህወሓት በፕሬቶሪያ ባደረጉት የዘላቂ ተኩስ ኡቁም ስምምነት ከቆመ ከጥቂት ወራት በኋላ ነው በአማራ ክልል አዲስ ግጭት የተቀሰቀሰው።
በክልሉ በመንግስት እና በፋኖ ሀይሎች እተካሄደ በሚገኝው ውጊያ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደርሶ ድጋፍ ለማድረግ ወደ ግጭት ቀጠናዎቹ መሻገር አዳጋች መሆኑን አቶ መስፍን ይናገራሉ፡፡
በቅርቡ በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ አካባቢ ከፍተኛ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እርዳታ ለማድረስ ማህበራችን ተንቀሳቅሶ ነበር፤ ነገር ግን ዋናው ችግር ያለበት ቦታ መድረስ ባለመቻላችን ተሸከርካሪዎቻችን በርካታ ጊዜትን መንገድ ላይ ቆይተው የወሰድናቸውን ድጋፎች ሌላ ቦታ አራግፈን ለመመለስ ተገደናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ችግሩ ከቦታ ቦታ ቢለያም ከአማራ ክልል ባለፈ በኦሮሚያ እና በአንዳንድ የደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል እንደሚስተዋል ተነግሯል፡፡
የአለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበር በአለም አቀፍ ደረጃ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ውግንና የሌለው በግጭት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ህይወት ለማዳን ብቻ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው የሚሉት አቶ መስፍን ባለፉት አመታት ይህ ተዘንግቶ ያጋጠሙን ፈተናዎች በርካታ ናቸው ነው ያሉት፡፡
እስካሁን ድረስ 15 የሚደርሱ የተቋሙ ሰራተኞች በተለያዩ አካላት የተገደሉ ሲሆን አሁንም ድረስ በእገታ ላይ የሚገኙ እና የት እንዳሉ የማይታወቁ ሰራተኞች እንዳሉ አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡
አሁንም በጥይት ተመተው ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ የሚገኙ የአምቡላንስ ሾፌሮች፣ የበጎ ፈቃድ ሰራተኞች አሉ፤ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል አርሲ አካባቢ ታፍነው የተወሰዱ ሁለት የማሕበሩ ሰራተኞች እስካሁን ድረስ የት እንዳሉ የት እንደደረሱ አይታወቅም ብለዋል፡፡
ታጋቾቹ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ ሲገናኙ የቆዩ ቢሆንም አሁን ላይ ግንኙነቱ በመቋረጡ ቤተሰቦቻቸው በስጋት እና ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ኃላፊው አክለው ገልጸዋል፡፡
የትኞቹም ሰብዓዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ሕጻናትና ሴቶች፣ ጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች የጥቃት ሰለባ መሆን የለባቸውም፤ ይህ አይነት ድርጊት የአለም አቀፍ ህግን የሚጻረር ነው ሲሉ ኃላፊው አሳስበዋል።
በተጨማሪም ባለፉት አራት እና አምስት አመታት እንደ ሀገር ያስተናገድናቸውን የተለያዩ ግጭቶች እና የሰላም መደፍረሶች ተከትሎ ምግብ፣ መጠለያ፣ ህክምና እና ሌሎች ድጋፎችንም የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነበር፤ ሆኖም በተደጋጋሚ ያስተናገድናቸውን ጥቃቶች ተከትሎ ማሕበሩ በደህንነት ስጋት ምክንያት የአቅሙን ያህል ተንቀሳቅሶ መስራት ፈታኝ ሆኖበት ቆይቷል ነው የተባለው፡፡
ትግራይ ክልልን በተመለከተ በጦርነቱ የወደሙ ጽህፈት ቤቶች እና የመድኃኒት መደብሮች ድጋሚ እንዲደራጁ እንዲሁም የወደሙ አምቡላንሶች እንዲተኩ ማሕበሩ ሰላም ከተመለሰ በኋላ ጥረት እያደረኩ ነው ብሏል፡፡
ነገር ግን ከውድመት ደረጃው ከፍተኛነት አንጻር አሁንም ተጨማሪ የአጋር አካላትን ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በአሁኑ ወቅት መጠነኛ መሻሻሎች ቢኖርም ሰራተኞች በደህንንት ስጋት ምክንያት ግጭት ወዳለባቸው አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ከከፍተኛ ፍርሀት እና ጭንቀት ጋር እንደሚያመሩ ተነግሯል፡፡
አሁንም በማሕበሩ አለማ እና አገልግሎት ዙሪያ የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ታጣቂዎች እና የትኛውም አካል ተቋሙ ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ የዘለለ የብሔር፣ የፖለቲካ እና የሀይማት ውግንና የሌለው መሆኑን ተርደተው ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠብ የተወሰዱ አምቡላንሶችም እንዲመለሱ የማሕበሩ የሰብዓዊ ዲፕሎማሲና የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ መስፍን ደረጄ ተማጽነዋል፡፡