መንግስት የሂዩማን ራይትስ ዋችን ሪፖርት ውድቅ አደረገ
ሂዩማን ራይትስ ዋች ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በምዕራብ ትግራይ በግዳጅ ማፈናቀልና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ የሚል ሪፖርት አውጥቶ ነበር
ሪፖርቱን መሰረተ-ቢስ ያለው መንግስት ፖለቲካዊ ተልዕኮ አለው ብሏል
ሂዩማን ራይትስ ዋች ከቀናት በፊት ከሰላም ስምምነቱ በኋላም በምዕራብ ትግራይ ብሄርን መሰረት ያደረገ በግዳጅ ማፈናቀል እየተፈጸመ የሚል ሪፖርት አውጥቶ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን መርምሮ በአፋጣኝ ተጠያቂነት እንዲያሰፍን የጠየቀው የሰብዓዊ መብት ተቋሙ፤ ተጎጅዎች፣ የአይን እማኞችንና የረዲኤት ሰራተኞች ጨምሮ 35 ሰዎችን አነጋግሮ ባወጣው ሪፖርት ነው።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ይህን ሪፖርት "አካባቢን የመረጠ" እና ተቀባይነት የሌለው ሲል ውድቅ አድርጎታል።
ሪፖርቱን መሰረተ-ቢስ ያለው ሚንስቴሩ፤ በሰብዓዊ መብት ሽፋን የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮን ለማሳት ዓላማ ያደረገ በሆኑ አልቀበለውም ብሏል።
"በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ግጭት በርካታ አካባቢዎችን ለጉዳት ያጋለጠ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ የተወሰነ አካባቢን መርጦ ደጋግሞ ሪፖርት በማዘጋጀት በሰብዓዊ መብት አጀንዳ ሽፋን የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮዉን ለማሳት ዓላማ ያደረገ በሆኑ ተቀባይነት የለውም" በማለት አብራርቷል።
የሪፖርቱ ይዘት ላይ ጥያቄም ያነሳ ሲሆን፤ ምርመራ ያልተደረገበት እና በበቂ ማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ ተአማኒነት እንደሚጎድለው ገልጿል።
በአጠቃላይ ሪፖርት "የተዛባና በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የማይይልጽ" ነው ተብሏል።
መንግስት በመግለጫው ግጭት ቀስቃሽና ሀገሪቱ እያደረገች ያለውን የእርቅና ምክክር ሂደት የሚያደናቅፍ አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው ሪፖርት ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብሏል።
በመግለጫው የሰሜኑ ጦርነት በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ጉዳት ያደረሰ ቢሆንም "አንድ አከባቢን ለይቶ በምረጥ" ሪፖርት መውጣቱ የድርጅቱን ድብቅ አጀንዳውን ያሳየ ነው ሲልም አክሏል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሞ አልታገስም ያለው መንግስት፤ በሰሜኑ ጦርነት ተፈጸሙ የተባሉ ጥሰቶችን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት ጥምር የምርመራ ቡድን እንዲያጣሩ መደረጉንና ለማስተካከያ ያቋቋመውን ግብረ-ኃይል ለአብነት ጠቅሷል።