አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጥምረት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድን "የአለም የሰላም መሪ" ሲል አደነቀ
የተመድ የሰብአዊ መብት ምክር ቤት 52ኛ ጉባኤ በጄኔቫ ሲካሄድ ነው ጥምረቱ የኤምሬትሱን ፕሬዝዳንት ያወደሰው
ከ200 በላይ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የሚኖሩባት ኤምሬትስ የአለም ወንድማማችነትን የሚያጎለብቱ ስራዎችን እየከወነች ነው
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በአለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጥምረት አድናቆት ተችሯቸዋል።
ኤምሬትስ 4ኛ ዙር የሰብአዊ መብት ሪፖርቷን በጄኔቫ በተካሄደው የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክርቤት 52ኛ ጉባኤ ላይ አቅርባለች።
የአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጥምረትም በዚሁ ወቅት የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጥረቶችን እየመሩ ይገኛሉ ብሏል።
ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የዘር መድልኦ እንዳይኖር እና ጽንፈኝነት እንዲወገድ የከወኗቸውን ስራዎችም የሚደነቁ መሆናቸውን ነው የገለጸው።
በተለይ የሰዎችን አብሮነት እና ወንድማማችነት የሚያጠናክሩ እና ልዩነትን የመቀበል ፍላጎት የሚያዳብሩ ተግባራትን በአጭር ጊዜ ውስጥ መከወናቸውንም በማንሳት።
በአለም አቀፍ ደረጃ የወንድማማችነት ቀን እንዲከበር ፕሬዝዳንቱ ያቀረቡት ሃሳብ በመንግስታቱ ድርጅት ተቀባይነት ማግኘቱንም ጥምረቱ በጄኔቫው ጉባኤ አብራርቷል።
ኤምሬትስ ፍትህ የሰፈነባት፣ እኩልነትና የሰው ልጅ ክቡርነት የተረጋገጠባት እንድትሆን የፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ ሚና በጉልህ የሚነሳ ነው ብሏል ጥምረቱ።
ከ200 በላይ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች በነጻነት የሚኖሩባት ኤምሬትስ የአለም መዲና ሆና እንድትጠቀስ የሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አስተዳደር በአርአያነት የሚጠቀስ ስራን መከወኑንም በማውሳት።
ሀገራት በእኩልነት እና ከመድልኦ በጸዳ መልኩ ችግሮችን የመፍታትና ሰላም የማስፈን ጥበብን ከአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሊማሩ እንደሚገባም ነው የአለማቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጥምረት የጠቆመው።
የሴቶችን መብት በማስከበር ረገድም “የኤምሬቶች እናት” ተብለው የሚጠሩት ሼይካ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ በአለማቀፍ ጥምረቱ ተደንቀዋል።
ኤምሬትስ የሰው ልጆች ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ በርካታ ለአለም ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራትን በፕሬዝዳንቷ ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ በኩል ተግባራዊ እያደረገች ነው።