ተጨማሪ 61 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 61 ሰዎች ኮሮና ተገኘባቸው
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገው 3 ሺ 757 የላብራቶሪ ምርመራ 61 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ምርመራው ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የተለያዩ የማህረሰብ ክፍሎች፣ከጤና ተቋማት፣በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ናሙና ተወስዶ የተከናወነ ነው፡፡
በምርመራው መሰረትም አጠቃላይ የቫይረሱ ታማሚዎች ቁጥር 494 ደርሷል እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ፡፡
አዲሶቹ የቫይረሱ ታማሚዎች ከ15 እስከ 70 አመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ 43ቱ ወንድ 18ቱ ደግሞ ሴት ናቸው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በሃገሪቱ አራት ክልሎችም ተገኝተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተገኙት 48ቱ ናቸው፡፡ ከ48ቱ 5ቱ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው ሲሆን 43ቱ ደግሞ ምንም ዓይነት ንክኪም ሆነ የውጭ ሃገራት የጉዞ ታሪክ የላቸውም፡፡
10ሩ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች በሚገኙ የጅግጅጋ እና የዱብቲ ለይቶ ማቆያዎች የነበሩ ናቸው፡፡ ከ10ሩ 7ቱ የውጭ ጉዞ ታሪክ የነበራቸው መሆኑን ተከትሎ በጅግጅጋ ተለይተው እንዲቆዩ የተደረጉ፤ 3ቱ ደግሞ ቀደም ሲል በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የነበራቸውና በአፋር ዱብቲ ለይቶ ማቆያ የነበሩ ናቸው፡፡
ሁለቱ ሰዎች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የቡራዩና የሰበታ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ አንዱ ታማሚ ደግሞ በአማራ ክልል የተገኘና የውጭ ጉዞ ታሪክ የነበረው መሆኑን ተከትሎ በደሴ ለይቶ ማቆያ የነበረ ነው፡፡
ሁለቱ የኦሮሚያ ታማሚዎች የንክኪም ሆነ የውጭ ጉዞ ታሪክ የላቸውም፡፡
በአጠቃላይ በቫይረሱ መያዛቸው ባለፉት 24 ሰዓት በምርመራ ከተረጋገጠ ታማሚዎች ውስጥ 11ዱ የውጭ ሃገራት የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣5ቱ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የተነካኩ ቀሪዎቹ 45 ሰዎች ደግሞ ምንም ዓይነት የንክኪም ሆነ የውጭ ጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው፡፡
በሌላ መልኩ ትናንት ከአዲስ አበባ 14 ከአፋር 9 በድምሩ 23 ተጨማሪ ታማሚዎች አገግመዋል ያለው ሚኒስቴሩ አጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 151 መድረሱንም ገልጿል፡፡
የዛሬውን ሪፖርት በተመለከተ ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡