ባልተመረጠ መንግስት እንተዳደራለን ማለት በጣም አስቸጋሪ ይመስለኛል-ፕ/ር አንድሪያስ እሸቴ
እንደተባለው ከሁለት ዓመታት በማይበልጥ ጊዜ ምርጫው የሚደረግ ከሆነ ምርጫው ወረርሽኙ እያለ ይደረጋል ማለት ነው
ጉዳዩ የሁሉንም ደህንነትና ነጻነት የሚነካ፣የመንግስትን ጉልበትና ሃብት የሚጠይቅ በመሆኑ ዝግጅቱ ከወዲሁ መጀመር አለበት
ባልተመረጠ መንግስት እንተዳደራለን ማለት በጣም አስቸጋሪ ይመስለኛል-ፕ/ር አንድሪያስ እሸቴ
ከቀረበው የህገ መንግስት ትርጓሜ ጥያቄ ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከሁለት ዓመታት በማይበልጥ ጊዜ ምርጫ መካሄድ ይኖርበታል በሚል በሊቃውንቱ የቀረበው ሃሳብ መልካም ቢመስልም አንዳንድ ችግሮች እንደሚያስከትል ይታየኛል ብለዋል፡፡
ወረርሽኝኙ በተጠቀሱት አመታት የሚወገድ አይደለም ያሉት ፕሮፌሰሩ ሊቃውንቶቹ ባሉት ጊዜ ምርጫው ይደረግ ከተባለ ምርጫው ወረርሽኙ እያለ ይደረጋል ማለት ነው፤ወረርሽኙ እስካልጠፋ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም የሚል ግምት ካለ ደግሞ ባልተመረጠ መንግስት ለዓመታት መኖር ይኖርብናል ማለት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ክትባት ተገኝቶለት ተመርቶ ለህዝብ እስከሚደርስ እና በወረርሽኙ ከደረሱ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ችግሮች ማገገም እስኪቻል ድረስ ዓመታትን እንደሚፈጅም አስቀምጠዋል፡፡
ይህ ደግሞ ትልቅ ችግር ነው እንደ ፕሮፌሰሩ አባባል፡፡
ለረዥም እና ላልተወሰነ ጊዜ ያም በመንግስት በሚወሰን ባልተመረጠ መንግስት እንተዳደራለን ማለቱም በጣም አስቸጋሪ ይመስለኛል ያሉም ሲሆን ማናችንም ከህግ ውጪ የሆነ መንግስት ለአመታት ይገዛናል ሲባል እንሰጋለን ብለዋል ሃሳቡ በህዝብ ዘንድ ላይዋጥ እና ተቀባይነት ላይኖረው እንደሚችል በመጠቆም ፡፡
ከደረሰብንን ከፍተኛ አደጋ ለመሻገር ብዙ ዝግጅት መከራከር፣ጥንቃቄ አድርገን እንዴት መሰባሰብና ምርጫውን ማካሄድ በምን ዓይነት ሚዲያ መጠቀም እንደምንችል ማወቅ ይጠይቃል ያሉም ሲሆን ከጤናም ከነጻነትም አኳያ የተሟላ እና ነጻ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅቱ ቀላል እንደማይሆንም ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩ የሁሉንም ደህንነትና ነጻነት የሚነካ፣የመንግስትን ጉልበትና ሃብት እጅግ የሚጠይቅ በመሆኑ ዝግጅቱ ከወዲሁ መጀመር እንዳለበት እና ዝግጅቱም መንግስትም ተፎካካሪ ኃይሎችም ህዝብም የሚስማሙበት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ዴሞክራሲያዊ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓትን የምንከተል ከሆነ ጥያቄው ይፈታል የሚል የግል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት ፕሮፌሰሩ ከሊቃውንቱ የተለየ ያሉትንም ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
ሃሳቡም በአጼ ኃይለስላሴ የስልጣን ዘመን መጨረሻ ዋዜማ ላይ የደረሰውንና እጅግ አስከፊውን የወሎ ርሃብ መሰረት ያደረገ ሲሆን የአደጋውን ክብደትና መጠን፤ የህዝብ ምርጫና ሌሎች ነጻነቶች እንዲሁም መብቶች ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ለመረዳት በሚያስችል መልኩ ከሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ ችግሮች ጋር አጣጥመን እንመልከተው የሚል ነው፡፡
ፕሮፌሰሩ ልክ እንደ አስከፊው ርሃብ ሁሉ አሁን እንዳለው ዓይነት ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ የመንግስት ደራሽነትና ተጠየቅነት የበለጠ ነው ያሉም ሲሆን ወረርሽኙ ቢኖርም ነጻ ምርጫም ነጻ ጋዜጠኝነትም ያስፈልጋል ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
ይህ ማለት ምርጫው አሁን ይደረግ ማለት እንዳልሆነም እድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው ለሁለተኛ ጊዜ አስተያየታቸውን በሰጡበት ወቅት አስምረው ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት እና በህገ መንግስቱ የማርቀቅ ሂደት የተሳተፉት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ስላሴ እንዲህ ያሉ እና ከምርጫና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር የሚገጣጠሙ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙ ምን ይደረግ የሚለው ቢያከራክርም ላልተገመቱና ልዩ ለሆኑ ሁኔታዎች ሕገ መንግስዊ ድንጋጌ ማስያዝ አይገባም በሚል ተትቷል ብለዋል፡፡
እንደዚህ አይነት ችግር ሲጋጥም “የሕገ መንግስቱን አንቀጾች መተርጎምና ማፍታታት ይገባል”ያሉት አምባሳደር ታዬ አሁን ያሉት የጉባዔው አባላት ይህንን ማድረግ ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የአስፈጻሚው አካል የስልጣን ጊዜ ክፍተት እንዳይኖረው ለማድረግ ተሞክሯል ያሉም ሲሆን በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንትና በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መካከል ያለው የሥልጣን ዘመን በአንድ አመት ተለያይቶ ተከታታይነት ባለው መልኩ ስድስት እና አምስት አመት መደረጉ ለዚሁ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ህገ መንግስቱን በማርቀቅ ሂደት የተሳተፉ ህግ ባለሙያዎችና ምሁራንም ጉዳዩን በማስመልከት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡