“መመሪያው ገንዘብ አታውጡ አይደለም”-የባንኮች ማህበር
መመሪያው ከህዝብ የተደበቀ እንቅስቃሴ እና ግብይትን ከሚያደርጉት በስተቀር ብዙሀኑን የሚጠቅም ነው
ይበልጥ እንዲጠብቅና ከባንክ ውጪ አለ ያለው 113 ቢሊዬን ብር እንዲመለስም ጠይቋል
“መመሪያው ገንዘብ አታውጡ አይደለም”-የባንኮች ማህበር
የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር (Ethiopian Bankers Association) ከጥሬ ገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ በብሄራዊ ባንክ የወጣውን አዲስ መመሪያ በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫን ሰጥቷል፡፡
መመሪያው ማህበሩ አጠናሁ ያለውን ጥናት መሰረት አድርጎ የወጣ ነው፡፡ በጥናቱ የተቀመጡ ምክረ ሃሳቦችም በመመሪያው አካልነት እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
ቀደም ባሉት አመታትም መመሪያው እንዲወጣ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ነበሩ ያለው ማህበሩ በቂም ባይሆኑም ባሉት አማራጭ የክፍያ ስርዓቶች የመጠቀሙ ነገር አናሳ መሆንን በገፊ ምክንያትነት ያስቀምጣል፡፡
የአገልግሎት ስርዓቱን ማዘመን፣ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግና ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳውን ማላቅም ጥናቱን ለማድረግ እና የሃገሪቱ የገንዘብ ስርዓት ተቆጣጣሪ አካል መመሪያውን እንዲያወጣ ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ ምክንያት መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡
“በሃገሪቱ ያለው የባንኮች፣ የቅርንጫፎች እና የወኪሎች ቁጥር እንዲሁም ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅማቸው እያደገ መጥቷል፤ አጠቃላይ የቅርንጫፍ ባንኮች ቁጥርም ከ5 ሺ በልጧል” ያሉት የማህበሩ ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትና ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አቤ ሳኖ የቁጥሩና የአገልግሎቱ ተደራሽነት መስፋት ከእነሱ (ከባንኮቹ) ውጪ የሚንቀሳቀሰውን የጥሬ ገንዘብ መጠን ሊቀንሰው እንዳልቻለው ገልጸዋል፡፡
ከ5 ዓመታት በፊት ማለትም እ.ኤ.አ በ2016 ከባንክ ውጭ ሲዘዋወር የነበረው 63 ቢሊዬን ጥሬ ብር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት (2020)113 ቢሊዬን ብር ደርሷል እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፡፡
ይህ ሆኖ ሳለ አሁንም ህብረተሰቡ ጥሬ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ መገልገሉ አልቀረም፡፡ በቀረቡ የቼክ፣ የሲፒኦ፣ የከአካውንት ወደ አካውንት እና ሌሎች የክፍያ አማራጮችን የመጠቀሙ ነገርም እንደቀጠለ ነው፡፡ በኤሌክትሮኒክስ ግልግሎቶችን የመጠቀሙ ነገር እንዲህ ፈቀቅ ባላለበት ሁኔታ አሁንም በብር የመገልገል ፍላጎቱ እየጨመረ ነው፡፡
“ይህ መቼ በአገልግሎት እንዘምናለን የሚለውን ጥያቄ ያከብደዋል” የሚሉት አቶ አቤ “የመመሪያው መውጣት ይህንን ለመመለስ ነው” ይላሉ፡፡
የሃገሪቱ ባንኮች ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ተወዳዳሪ ለመሆን በሚያስችሏቸው ዘመን አፈራሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለመዘመን የሚያደርጉትን ጥረትም ውጤት አልባ ያደርጋል፡፡
ማህበሩ በመግለጫው መመሪያው “ከህዝብ የተደበቀ እንቅስቃሴ እና ግብይትን ከሚያደርጉት በስተቀር ብዙሀኑን የሚጠቅም ነው፤ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ይቀንሳል፣የህዝብን ኑሮ ይቀይራል፣ቁጠባን ኢንቨስትመንትንና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያበረታታል” ብሏል፡፡
አሁን ባለዉ ሁኔታ ሁሉም ባንኮች በተሻለ ደረጃ እና “ሊኩዲቲ” ወይም የገንዘብ አቅም ላይ የሚገኙ ናቸው ያለም ሲሆን መመሪያው እንዲያውም ዘግይቷል ብሎ እንደሚያምንና የሚሰሙ ስጋቶች ተገቢ እንዳልሆኑ ገልጿል፡፡
እንደ ሃገር እና እንደ ህዝብ ማደግ የግድ መሆኑን ተከትሎ አገልግሎቱን ለማዘመን ከመሻትና ህብረተሰቡ እንዳይወናበድ ሂደቱን በህግና ስርዓት ከመደገፍ በስተቀር ሌላ ነገር የለውምም ብሏል፡፡
መመሪያው በግለሰብ ደረጃ በቀን እስከ 2 መቶ ሺ በወር እስከ አንድ ሚሊዬን፤ በተቋም ደረጃ ደግሞ በቀን 3 መቶ ሺ በወር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዬን የሚደርስ ጥሬ ገንዘብ ከባንኮች እንዲወጣ ይፈቅዳል፡፡
ይህ ማለት ግን እንደ ማህበሩ ገለጻ “ማንኛውም አካል ከተጠቀሰው ውጭ ያለውንና የሚፈልገውን ያህል የገንዘብ መጠን ማንቀሰቀስ አይችልም ማለት አይደለም፤ ይልቁንም ሌሎች ቀደም ሲል የተጠቀሱ የክፍያ አማራጮችን ተጠቅሞ ገንዘቡን ማዘዋወር፣ክፍያን መፈጸም እና ሌሎቹንም ግልጋሎቶች ማግኘት እንዲችል የሚያበረታ ነው”፡፡
መመሪያው ከባንኮች ውጪ የትኛውንም አካል ይመለከታል፡፡ በተለየ ሁኔታ ከተጠቀሰው ገንዘብ በላይ የሚያስፈልግ ከሆነ እና ባንክ ማስቀመጥና መክፈል የማይቻልበት ሁኔታ ካለ ግን አስፈላጊነቱ ተረጋግጦ ሊታይ ይችላል፡፡
መመሪያው መልዕክት የማስተላለፍ ያህል ነው፤ እንዲወጣ ብቻም ሳይሆን ቁጥጥሩ እንዲጠብቅም እንፈልጋለን” የሚለው ማህበሩ ከባንክ ውጪ አለ ያለው 113 ቢሊዬን ብር እንዲመለስ እና በመመሪያው የተጠቀሰው የጥሬ ገንዘብ መጠን ዝቅ ብሎ በቀን ከአስር ሺ በታች እንዲሆን መንግስትን ስለመጠየቁ አስታውቋል፡፡ “ይህ ብር በመቀየር የሚሆን ነው” ያለም ሲሆን ጥያቄው ይመለሳል ብሎ እንደሚጠብቅም ገልጿል፡፡
በመግለጫው የዳሽን፣የአዋሽና የዘመን ባንክ ፕሬዝዳንቶች ተሳትፈዋል፡፡