የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል የተናጠል ምርመራ አደርጋለሁ ማለቱን ኢትዮጵያ ተቃወመች
የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል የተናጠል ምርመራ አደርጋለሁ ማለቱን እንደሚቃወም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ኮሚሽኑ ብቻውን በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶችን እመረምራለሁ ማለቱ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡ ነገርግን ሚኒስቴሩ ህብረቱ ምርመራ ማድረግ ከፈለገ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጋራ ማካሄድ ይችላል ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ ለ3 ወራት ምርመራ እንደሚያካሂድ ከሰሞኑ የገለጸ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግስት ግን በትብብር እንጅ ኮሚሽኑ ብቻውን የማካሄድ ስልጣን እንደሌለው አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት፤ የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ብቻዬን አካሂዳለሁ ያለውን የምርመራ ሂደት በአስቸኳይ እንዲያቋርጥም ጠይቋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል የሚያደርገውን ምርመራ የፊታችን ሀሙስ ሰኔ 10፤ 2013 በይፋ እንደሚጀምርም አል ዐይን ከሰሞኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ተፈጽሟል የተባለውን የመብት ጥሰት በጋራ ለመመርመር ተስማምተው ነበር፡፡